ቀዳሚ ገጽ » » ሆሳዕና የዐብይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት

ሆሳዕና የዐብይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት

Written By bahir dar city foot ball club on Thursday, April 2, 2015 | 11:51 AM

ሆሣዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራው ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መገቢያ ዋዜማ ነው።
ሆሣዕና አስቀድሞ ካለው ረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተክርስቲያን የበዓል ቀን እንደሆነ ይታወቃል። ይህን ስም በዚሁ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‘ሆሣዕና በአርያም’’ ‘ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት’’ ‘ዕለተ ሆሣዕናሁ አርዓየ… ‘ ወዘተ. በማለት ሆሣዕና የሚለውን ቃል ቅዱስ ያሬድና ሌሎችም አባቶች በየቦታው እየጠቀሱና እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተረከ ስለሚዘምር ይህ ሰንበት በጌትነትና በክብር በውዳሴና ቅዳሴ ሆሣዕና በአርአያም እየተባለ በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በከብር ሲገባ ለሰጣቸው ለተቀደሰ ሰላሙና ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሌላ ቀን እንደ ተራ ሰው ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ይገባ ነበር፡፡ በዚህ ቀን ግን የአይሁድ ንጉሥ ሆኖ በክብር ገባ፡፡ ከቢታንያ ተነሥቶ ደብረ ዘይት ሲደርስ ከሐዋርያቱ ሁለቱን በቤተፋጌ ሰው ተቀምጦባት የማያውቅ ውርንጭላ እንዲያመጡለት ላካቸው፡፡ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሒዱ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእር ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም አምጡልኝ፡፡ ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ" አላቸው፡፡ ማቴ.21፡1-17

ወደ ቤተፋጌም ሄደው አህያዪቱን አገኙአት፡፡ ሲፈቱአትም ሳለ ባለቤቶቹ መጡባቸውና አስቆሟቸው፡፡ እነርሱም ኢየሱስ እንደፈለጋት ነገሩአቸው፡፡ ባለቤቶቹ ይህንን ሲያውቁ ተውአቸው፡፡ ሐዋርያትም የአህያዪቱን ውርንጭላ ፈትተው ወደ ኢየሱስ ወሰዱ፡፡ አጠገቡም ሲደርሱ ልብሳቸውን በአህያዪቱ ውርንጭላ ላይ አንጥፈው ኢየሱስን አስቀመጡት፡፡
ለምን ዘንባባ ያዙ ቢባል፤ ዘንባባ እሾሃም ነው ፤አንተም የኃይል የድል ምልክት አለህ ሲሉ፤በሌላም በኩል ዘንባባ እሳት ለብልቦ ይተወዋል እንጂ አይበላውም አንተም ባህርይህ አይመረመርም ሲሉ፤አንድም ዘንባባ ረጅም /ልዑል/ ነው አንተም ባሕርይህ ልዑል ነው ሲሉ ዘንባባ ይዘው ተቀብለውታል፡፡

የተምር ዛፍ ዝንጣፊ ነው ቢሉ፤ ተምር ፍሬው አንድ ነው አንተም ባህርይህ አንድ ነው ሲሉ፡፡አንድም፤ተምር ልዑል/ረጅም/ ነው አነተም ልዑለ ባህርይ ነህ ሲሉ፡፡ አንድም፤የተምር ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው በቀላሉ መለቀም አይቻልም ፤የአንተም ምስጢር አነተ ካልገለጠከው አይመረመርም ሲሉ ነው፡፡

የወይራ ዛፍ ዝንጣፊ ነው ቢሉ፤ ወይራ ጽኑዕ/ ጠንካራ/ ነው አንተም ጽኑዓ ባህርይ ነህ ሲሉ፤አንድም ወይራ ለመስዋዕት ይሆናል፤ አንተም መስዋዕት ትሆናለህ ሲሉ፤አንድም ወይራ ዘይቱ ለመብራት ይሆናል አንተም የዓለም ብርሃን ነህ ሲሉ ይህንን ይዘው አያመሰገኑ ተቀበሉት፡፡

ልብሳቸውንም ማንጠፋቸው፤ እንኳን አንተ የተቀመጥክባት አህያ እንኳን መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ ልብሳቸውን አነጠፉለት፡፡ እነዚያ ያላመኑ አይሁድ ለተቀመጠባት አህያ ይህንን ያህል ክብር ከሰጡ፤ በድንግልና ጸንሳ ለወለደችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምን ያህል ክብር ልናድረግለት ይገባን ይሆን?፡፡         

“የጽዮን ልጅ ሆይ አትፍሪ እነሆ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ይመጣል” ዘካ.9፡9 የሚለው የዘካርያስ ትንቢት ተፈጸመ፡፡ ሕዝቡም ኢየሱስ በመምጣት ላይ እንዳለ ሲያውቅ ሊቀበለው ወጣ፡፡ አንዳንዶች ያልፍበት በነበረ መንገድ ልብሳቸውን እንዳንዶቹ ደግሞ የዘንባበ ዝንጣፊ ያነጥፉ ነበር፡፡ ከፊትና በኋላ ያሉት ደግሞ “ሆሳዕና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ” እያሉ በታላቅ ድምፅ ይጮሁ ነበር፡፡ ኢየሱስ በሕዝቡ እልልታና ደስታ ታጅቦ ሲገባ ተጠንቅቀው ይታዘቡትና ይመለከቱት የነበሩ ፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርቱን ዝም እንዲያሰኛቸው ተናገሩት፡፡ እርሱም ሕዝቡ ዝም ቢል ድንጋዮች እንደሚጮኹ አስታወቃቸው፡፡ ኢየሱስ ኢየሩሳሌምን ሲያያት አለቀሰላት፡፡ “አንቺ ኢየሩሳሌም ለሰላምሽ የሚያስፈልገውን ነገር ምነው አውቀሽ ቢሆን ኖሮ አሁን ግን ይህ ነገር ከዓይንሽ ተሰውሮብሻል ጠላቶችሽ በዙሪያሽ እንደ አጥር ከብበው በዚህም በዚያም አንቺን የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣል… ምክንያቱም እግዚአብሔር ሊያድንሽና ሊጐበኝሽ የመጣበትን ጊዜ ባለማወቅሽ ነው” እያለ ረገማት፡፡

መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ሰለ ደኅንተቷ ሊያሳስባት ፈልጐ ነው፡፡ በማያወላዳ መንገድ ንጉሷና መድኃኒቷ እንደሆነ ገለጸላት፡፡ ወደ ራሷ ተመልሳ ጸጋዋን እንድትቀበል የልቧን ድንዳኔ ትታ እርሱን እንድትሰማ አስጠነጠቃት፡፡ ግን አልተጠነቀቀችም፡፡ ለጊዜው በክብር ተቀበለችው፡፡ ከጥቂት ቀን በኋላ ግን ተወችው፤ በመስቀል ላይ ሰቀለችው፡፡ የደኅንነቷን ቀን ማወቅ ተሳናት፡፡ በዚህም ደግሞ ከብዙ ዓመታት በኋላ መዓት ወረደባት፡፡

ይህ የሚያሳዝን የኢየሩሳሌም ሥራ የእኛም ሥራ ነው፡፡ ኢየሱስን መድኃኒታችንን መቀበል አንፈልግም ወይም ተቀብለን በኃጢአታችን ከእኛ እንዲርቅ እናደርገዋለን፡፡ በቅዱስ ቁርባን ወደ እኛ ሲመጣ በደስታ እንቀበለዋለን፡፡ ትንሽ ቆየት ብለን ደግሞ እናዋርደዋለን፡፡ ከእርሱ ጋር እንጣላለን፡፡ ከኃጢአት ጋር ጓደኝነት እንይዛለን፡፡ በኃጢአት ስንወድቅ እርሱን እንደገና እንሰቅለዋለን፡፡ ኢየሱስ እኛን “አቤት በዚህ ቀን ለደኅንነትህ የሚደረገውን ብታውቅ ኖሮ …፣ ይህ ሁሉ ከዓይንህ ተሰውሮብሃል ማወቅን አልፈለግህም፡፡ ይህን እወቅ ግን አንድ ቀን …” እያለ አዝኖ ይፈርድብናል፡፡ ይህንን በማሰብ ሲመጣና ሲናገረን እምቢ አንበለው አናባርረው፡፡ በኋላ እርሱ ቂም ይዞ እምቢ እንዳይለና እንዳያባርረን ደኅንነታችንን ራሳችን አናጥፋት፡፡



የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
ወእንዘ ሰሙን በዓለ ፋሲካ ቀርቡ አርዳኢሁ ለአምላከ ጽድቅ ኀበ ደብረ ዘይት ሙራደ ዓቀብ ሀገረ እግዚአብሔር ወተቀበልዎ ሕዝብ ብዙኃን አዕሩግ ወሕፃናት ነሢኦሙ አዕፁቀ በቀልት እንዘ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም ተፅዒኖ ዲበ ዕዋል ቦአ ሀገረ ኢየሩሳሌም በትፍሥሕት ወበሐሴት ይሁቦሙ ኃይለ ወሥልጣነ፡፡…..
ትርጉም: “በፋሲካ በዓል ሰሞን የእውነት አምላክ ደቀ መዛሙርት ወደ ደብረ ዘይት ቀረቡ፤ በሀገረ እግዚአብሔር (ኢየሩሳሌም) አቀበቱ ላይ ብዙ አረጋውያንና ሕፃናት የዘንባባ ቅጠል ይዘው ሆሣዕና በአርያም እያሉ ተቀበሉት፣ በአህያ ውርንጫ ላይ ተጭኖ በፍጹም ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። ለእነዚህ ኃይልና ሥልጣንን ይሰጣቸዋል።
መልዕክታት
ዕብ.8÷1-ፍጻ. ከተናገርነውም ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፡፡ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፤ እርስዋም በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር የተተከለች ናት፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)
1ኛ ጴጥ.1÷13 ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና ነቅታችሁ ኑሩ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ፡፡  (ተጨማሪ ያንብቡ)
ግብረ ሐዋርያት
የሐዋ.8÷26-ፍጻ. የእግዚአብሔር መልአክም ፊልጶስን ተናገረው፤ እንዲህም አለው÷ “በቀትር ጊዜ ተነሣና በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚያወርደው በምድረ በዳው መንገድ ሂድ፡፡” ተነሥቶም ሄደ፡፡” እሆም÷   (ተጨማሪ ያንብቡ)
ምስባክ
መዝ.80÷3 "ንፍሑ ቀርነ በዕለት ሠርቅ፡፡ በእምርት ዕለት በዓልነ፡፡ እስመ ሥርዓቱ ለእስራኤል ውእቱ"
ትርጉም፦ በመባቻ ቀን በታወቀችው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ፤ ለእስራኤል ሥርዐቱ ነውና÷ የያዕቆብም አምላክ ፍርድ ነውና፡፡
ወይም
መዝ.80÷2 "እምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሓተ፡፡ በእንተ ጸላዒ፡፡ ከመ ትንሥቶ ለጸላዒ ወለገፋዒ፡፡"
ትርጉም፦ ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ፡፡ ስለ ጠላት÷ ጠላትንና ግፈኛን ታጠፋው ዘንድ፡፡
ወንጌል
ዮሐ.12÷1-11 ፋሲካ ከሚውልበት ከስድስተኛው ቀን አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ያስነሣው አልዓዛር ወደ ነበረበት ወደ ቢታንያ መጣ፡፡(ተጨማሪ ያንብቡ)
ቅዳሴ
ቅዳሴ ዘጎርጎርዮስ፡፡

ምንጭ
·         ማሕበረ ቅዱሳን ደረገጽ
·         መናገሻ ጽጌ ሰ/ት/ቤት ገጽ

·         ቃለ ሕይወት(አጭር ግጻዊ)

0 አስተያቶች:

Post a Comment

Facebook Twitter Addthis Google+