ቀዳሚ ገጽ » » .“ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ?(መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ)

.“ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ?(መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ)

Written By bahir dar city foot ball club on Sunday, April 12, 2015 | 11:30 PM

“ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚኽ የለም (ሉቃ 24፡5).....
                                           አዘጋጅ መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (PHD Candidate) 
ይህ የትንሣኤ በዓል ሞት የተሸነፈበት፣ መቃብር የተረታበት፣ ሕይወት ያገኘንበት ታላቅ በዓል ነውና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሞት አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን፣ በሞቱ ሞትን ድል መንሣቱን፣ ሙስና መቃብር መጥፋቱን፣ ዓለም በብርሃን መመላቱን ትመሰክራለች፡፡
የባሕርይ አምላክ ወልደ እግዚአብሔር ለአዳም በሰጠው ተስፋ መሠረት ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በመስቀል ተሰቅሎ ዓለምን እንደሚያድን፤ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊትም በመቃብር ዐድሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ የትንሣኤውን ብርሃን እንደሚገልጽ ነቢያት ቀድመው ትንቢትን ይናገሩ ነበር ለምሳሌ ቅዱስ ዳዊት አምላክ የሞትን ማሠሪያ በጥሶ እንደሚነሣ በመዝ 11፡5 ላይ አሁን እነሣለሁ ይላል መድኃኒትን አደርጋለሁ፥ በላዩም እገልጣለሁ በምድር ላይ እንደ ተፈተነ ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ ብር። የእግዚአብሔር ቃላት የነጹ ቃላት ናቸው” በማለት ትንቢትን ይናገር ነበር፡፡

ክብር ይግባውና ለአዳም በሰጠው ተስፋ መሠረት ወልደ እግዚአብሔር ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ተወልዶ በሚያስተምርበትም ጊዜ 3 ቀንና 3 ሌሊት በከርሠ መቃብር ዐድሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ እንደሚነሣ ያስተምር ነበር፡፡ ጥቅሶቹም
► “ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል” (ማቴ 12፡40)
► “የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል በሽማግሌዎችም በካህናት አለቆችም በጻፎችም ሊጣል ሊገደልም በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ይገባዋል” (ሉቃ 9፡21)
► “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ” (ዮሐ 2፡19)
ያለው ሊፈጸም አምላክ በከርሠ መቃብር 3 ቀንና 3 ሌሊት ዐድሯል፡፡
የዚኽም አቈጣጠር ሁለት ዐይነት ነው የመጀመሪያው “መዓልት ይስሕቦ ለሌሊት ወሌሊት ይስሕቦ ለመዓልት” (ቀን ሌሊትን ሌሊት ቀንና ይስባል) በሚለው የአቈጣጠር ዘዴ ጌታ ቅድስት ነፍሱን ከሥጋው ከለየ በኋላ ዐርብ በሠርክ ወደ መቃብር ስለወረደ ዐርብ እንደ አንድ ቀን ሲቈጠር፤ ቅዳሜ ያው አንድ ቀን፣ እሑድ ደግሞ መንፈቀ ሌሊት ስለተነሣ እሑድ እንደ አንድ ቀን ይቈጠራል
ሌላው አቈጣጠር ደግሞ ዕለት የሚለው ፍቺ አንድ እጅ ብርሃን አንድ እጅ ጨለማን ያካተተ ነው፤ ሰለዚህ በዚህ ተመርጒዘን ካየነው
► የስቅለት ዕለት ዐርብ ከጠዋት እስከ ስድስት ሰዓት ብርሃን ስለሆነ አንድ እጅ ብርሃን
► ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጨለማ ስለኾነ አንድ እጅ ጨለማ
► በሠርክ ደግሞ ብርሃን ሆኗል አንድ እጅ ብርሃን
► ቅዳሜ ደግሞ ሙሉ ቀን ሙሉ ሌሊት ስለሆነ አንድ እጅ ብርሃን አንድ እጅ ጨለማ
► ጌታ የተነሣው እሑድ ሌሊት ስለሆነ አንድ እጅ ጨለማ ነበር፡፡
ስለዚህ ሦስት እጅ ብርሃን ሦስት እጅ ጨለማ 3 መዓልት 3 ሌሊት ተብሏል፡፡
ጌታችን ለምን ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ዐደረ ቢሉ?
ሀ) 1) አዳምን 2) ሔዋንን 3) ሕፃናቱን እንዳደነ ለማስረዳት 3 ዕለት ዐደረ
ለ) 1) ለሥጋችን 2) ለነፍሳችን 3) ለደመ ነፍሳችን እንደካሰልን ለማስረዳት
ሐ) የሰው 3 ጠላቶች ይኽውም 1) ሞት 2) ፍዳ 3) ኀጢአትን እንዳጠፋ ለማጠየቅ ነው
ክብር ይግባውና ትንሣኤና ሕይወት የኾነው አምላካችን ክርስቶስ ሞትን ድል ነሥቶ በድንቅ ምስጢር መቃብሩ እንደተዘጋ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ያን ጊዜ ዓለም በብርሃን ተዋጠ፡፡ የፅንሰቱና የልደቱ ምስጢር ከትንሣኤው ምስጢር ጋር ይስማማል፤ ይኸውም በፅንሰቱና በልደቱ የእናቱ የቅድስት ድንግል ማርያምን ማኅተመ ድንግልና ሳይከፍት እንደተፀነሰና ሳይከፍት እንደተወለደ ሁሉ አሁንም በተዘጋ በተገጠመ መቃብር በድንክ አምላካዊ ጥበብ ረቂቅ ዘእምረቂቅ የሆነው አምላክ ተነሣ፡፡ ለዚህ ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሥርዐተ ቅዳሴዋ ላይ “ሃሌ ሉያ ዮሴፍ ወኒቆዲሞስ ገነዝዎ ለኢየሱስ በሰንዱናት ለዘተንሥአ እሙታን በመንክር ኪን” (ቅድመ ዓለም የነበረ ዓለምን አሣልፎ የሚኖረውን በድንቅ አምላካዊ ሥራ ከሙታን ተለይቶ የተነሣውን ጌታችንን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በበፍታ ገነዙት) በማለት ለልጆቿ የትንሣኤውን ታላቅነት እየመሠከረች “ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ” (ትንሣኤህን ለምናምን ለእኛ ብርሃንህን ላክልን ወደኛ) እያለች በፍጹም ደስታ ትዘምራለች፡፡
ዕለተ እሑድ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ የተነሣባት ዕለተ እሑድ የክርስቲያኖች ሰንበት ናት እናከብራታለን ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙር 117፡24 ላይ ስለዚች ዕለት እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን” በማለት ክብሯን መስክሮላታል፤ ስለዚህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የትንሣኤ ዕለት በቅዳሴ ጊዜ የሚሰበከው የዳዊት ምስባክ ይህ እንዲሆን አድርጋለች ፡፡ እሑድ የክርስቲያኖች ሰንበት መባሏ በዕለቷ አምላካችን ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቶባታልና ይኸውም
ሀ) ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ፈጥሮባታል (ዘፍ 1፡1)
ለ) በቅዱስ ገብርኤል አብሣሪነት በእመቤታችን ማሕፀን ዐድሮባታል (ሉቃ 1፡26)
ሐ) ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቶባታል (ዮሐ 20፡1)
መ) ለሐዋርያትም መንፈስ ቅዱስን ልኮ ሰማያዊ ሐብትን ሰጥቶበታል (የሐዋ 2፡1-4)
ሠ) ዳግመኛ ዓለምን ለማሳለፍና እኛንም ከሞት ሊያስነሣን የትንሣኤያችን በኲር ትንሣኤና ሕይወት የሆነው ጌታ በዚህች ቀን ተመልሶ ለፍርድ ይመጣልና እሑድ “የጌታ ቀን፣ ሰንበተ ክርስቲያን” ተብላለች (ራእ 1፡10)፡፡
የአምላክችን የክርስቶስ ትንሣኤን “ቅድስት” ተብሎ ይጠራል፤ ምንያቱም የጌታችን ትንሣኤ በ3 መልኩ ከነአልዓዛር ትንሣኤ ስለሚለይ ነው፡- ይኸውም
ሀ) ይኸውም የዕለት ሬሳ የኾኑት የኢያኢሮስ ሴት ልጅ፣ የመበለቲቱ ልጅ፣ የአራት ቀን ሬሳ እነአልአዓዛር ከሞት ቢነሡ አስነሽ እርሱን ሽተው ነው፤ ርሱ ግን በዮሐ 10፡17 ላይ “ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል፤ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ” እንዳለ የተነሣው በራሱ ሥልጣን ነውና፡፡
ለ) የነአልዛዓር ትንሣኤ እንደገና ሞትን ያስከትላል፤ ጌታችን ግን “ኢይመውት እምዝ ዳግመ” እንዲለው ሞትን የማያስከትል ፍጹም ትንሣኤ ነውና
ሐ) የነአልዓዛር ትንሣኤ እንደገና ሞተው ዳግመኛ ትንሣኤ ዘጉባኤን ሲጠብቁ አምላካችን ግን “ወአሕጸረ ዕድሜ ለርእሱ” እንዲለው ፈጥኖ ተነሥቷል በኲረ ትንሣኤ ነውና፤ በማለት የትንሣኤውን ምስጢር ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡
የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በብዙ ነገሮች ተመስክሯል፡፡ ይኸውም
► በራሱ በመድኀኔ ዓለም ሲሆን አስቀድሞ ለማርያም መግደላዊት፣ ለቅዱሳት አንስት፣ በመንገድ ሳሉ ለሁለቱ ከዚያም ሁሉም ባሉበት በዝግ ቤት ገብቶ “ሰላም ለእናንተ ይሁን…እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ” በማለት ሞትን በሞቱ ድል የነሣው ትንሣኤና ሕይወት የሆነው አምላክ ገልጾላቸዋል (ሉቃ 24፡37)፡፡
► በመላእክት ተመስክሯል፡፡ ይኸውም ሽቱ ይዘው ወደ መቃብሩ ለገሠገሡት ቅዱሳት ሴቶች ብርሃን የለበሱ ቅዱሳን መላእክት ተገልጸው “ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ” በማለት የአምላካቸውን ትንሣኤ መስክረዋል ሰብከዋል (ሉቃ 24፡1-7)
► ባዶው መቃብር ምስክር ነው፤ ዮሐንስና ጴጥሮስ ወደ መቃብሩ ገሥግሠው በኼዱ ጊዜ በባዶው መቃብር ስላገኙት ነገር ቅዱስ ወንጌል ሲጽፍ እንዲህ ይላል “ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፥ አየም፥ አመነም” ይላል (ዮሐ 20፡5-8) ዛሬ ወደ ኢየሩሳሌም በየዓመቱ ከየዓለማቱ የሚጓዙ ክርስቲያኖች ስፍር ቊጥር የላቸውም እነርሱም የሚሄዱት ዐፅም፣ ሐውልት ለማየት ሳይሆን ባዶውን መቃብር ጐብኝቶ አይቶ የሞትን መሸነፍ መዋረድ ድል መነሣት አይቶ አምላክን ለማመስገን ነው
► ይኽ ብቻ ሳይሆን እነ ማርያም መግደላዊት፣ ቅዱሳት አንስት፣ ከእግረ መስቀሉ ሥር የተነሡት 500 ሙታኖች፣ እስከ ዕለተ ምጽአት የሚነሡ ክርስቲያኖች ሁሉ ምስክር ናቸው (1ቆሮ 15፡6)፡፡
በሞቱ ሞታችንን የሻረው መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ ክብር ምስጋና ይግባውና “ትንሣኤና ሕይወት” ነውና ቅዱስ ጳውሎስ በ1ቆሮ 15፡20-21 ላይ “አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው” እንዳለ ሞት ተሸንፏል እኛም ሞተን አንቀርም ርሱ ዓለምን ለማሳለፍ ሲመጣ ከሞት አስነሥቶ መንግሥቱን ያወርሰናልና የትንሣኤ በዓል ለእኛ ለክርስቲያኖች የድል፣ የሰላም፣ የደስታ፣ የሕይወት፣ የማሸነፍ በዓል ነው፡፡
► “ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን” (ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ)
► “በዐቢይ ኀይል ወሥልጣን” (በገናና ኀይልና ሥልጣን)
► “ዐሠሮ ለሰይጣን” (ሰይጣንን ዐሰረው)
► “አግአዞ ለአዳም” (አዳምን ነጻ አወጣው)
► “ሰላም” (ፍቅር አንድነት ሆነ)
► “እምይእዜሰ” (ከእንግዲህስ)
► “ኮነ” (ሆነ)
► “ፍሥሐ ወሰላም” (ደስታ ሰላም) አሜን፡፡
እንኳን አደረሳችሁ፡፡
መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ

0 አስተያቶች:

Post a Comment

Facebook Twitter Addthis Google+