ቀዳሚ ገጽ » » ስቅለት

ስቅለት

Written By bahir dar city foot ball club on Thursday, April 9, 2015 | 11:54 PM

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐሙስ ማታ እንደተያዘ ሌሊቱን ሁሉ መከራ ሲቀበል አድሮ ዓርብ ጧት የአይሁድ ሽማግሌዎችና አለቆች ተሰብስበው ወደ ሹሙ ወደ ጲላጦስ ቤት ይዘውት ሔዱ፡፡
ከዚያም ይህ ሰው ከሕጋችን ጋር የማይስማማ ትምህርት ሕዝቡን ያስተምራልና እንደ ሕጋችን ሞት ይገባዋል፡፡ ንጉሥ ነኝ፣ እያለም ያታልላል በማለት በሹሙ ፊት ቀርበው ከሰሱት፡፡ ጲላጦስ ግን ብዙ ቢዋሹበትና ቢከሱት አላመናቸውም ነበር፡፡ ምክንያቱም መርምሮ በደል አላገኘበትምና ሊያድነው አስቦ ነበር፡፡ ግን ሊያድነው አልተቻለውም፡፡

ጲላጦስ ጌታችንን ሲመረምር ለብቻው አቁሞ መጠየቅ የሮማውያን ልማድ ነበርና አዳራሽ አስገብቶ ለብቻው የተከሰሰበትን ነገር ጠየቀው፡፡ አይሁድ ግን በዓለ ፋሲካ ደርሶባቸው ነበርና ስለ በዓሉ ክብር ሲሉ ወደ ፍርድ ቤት አልገቡም፡፡ ከውጪ ተሰብስበው እርስ በእርሳቸው እንደፈቃዳቸውና እንደምኞታቸው ጌታን ለመስቀል ያስቡ ነበር፡፡

ጲላጦስም ጌታን ለብቻው በጥያቄ ከመረመረው በኋላ ከአዳራሹ ወደ ውጭ ብቅ ብሎ በዚህ ሰው ለሞት የሚያበቃ በደል ወይም ምክንያት አላገኘሁበትም ያውላችሁ አላቸው፡፡ እነሱም ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሏልና ሞት ይገባዋል፡፡ €œስቀለው፣ ስቀለው እያሉ መለሱለት፡፡ እሱም እንደገና ለብቻው ጠይቆና መርምሮ የሚሞትበት በደል ስላላገኘበት ከአዳራሹ ወደ ውጭ ወጣና ውኃ አስመጥቶ በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ፡፡ ከዚህም ሰው ደም ንጹሕ ነኝ ሞት አልፈርድበትም እያለ ሐቁን መሰከረ፡፡

አይሁድ ግን ይህ ሰው ንጉሥ ሳይሆን ንጉሥ ነኝ ብሏል፤ ንጉሥ ነኝ የሚል ሁሉ የቄሳር ተቃዋሚ ጠላት ነው፡፡ የቄሳር ወደረኛ መሆኑን እኛ እየመሰከርን አንተ ግን የቄሳር ሹም ሆነህ ብትለቀው አንተ ታውቃለህ እያሉ ጲላጦስን አስፈራርተውታል፡፡ ጲላጦስም ይህን ሲሰማ በራሱ ላይ ክስ እንዳይመጣበት ጌታችንን አሳልፎ ሰጥቷቸዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ጌታችንን ወታደሮቹ ተቀብለው ወደ ሌላ አዳራሽ አስገቡት፡፡ ልብሱን ገፍፈው፣ ሌላ ቀይ ልብስ አልብሰው፣ የሾህ አክሊል በራሱ ላይ ደፍተው፣ ዘንግ በእጁ አስይዘው፣ ሎቱ ስብሐት €œንጉሥ ከሆንህ ለአንተ ስግደት ይገባል፡፡ ልብሰ መንግሥት ያምርብህ ይሆን? ክርስቶስ ከሆንህ ትንቢት ንገረንእያሉ ፊቱን ሸፍነው ራስ ራሱን በዘንግ እየመቱ ተሳለቁበት፡፡

ከያለበሱትንም ልብስ ገፍፈው የቀድሞ ልብሱን አልብሰው፣ መስቀሉን አሸክመው ወደሚሰቀልበት ቦታ ወደ ቀራንዮ ወሰዱት ሰቀሉትም

ጌታ በጲላጦስ ፊት ከቆመበት ቦታ ጀምሮ እስከ መካነ ትንሳኤው ድረስ በዕለተ ዓርብ የሆነውን ሁሉ እየተነበበና እየተተረከ ወደ ላይ ወደ ቀራንዮ ይገባል፡፡ በየጉዞው ላይ ጸሎት የሚደረጉባቸው ዐሥራ አምስት ምዕራፎችም አሉ፡፡ እነሱም:- ፍኖተ መስቀል ይባላሉ

ስለጌታችን ህማም ቅዱሳን አባቶች ምን አሉ 

የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ
 እንዲህ አለ  ታመመ፤ ሞትን ከተቀበለበት ከሥጋ ተዋሕዶ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ለሥጋውያን ሞተ፣ ባሕርየ  መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ በማኅፀን ካደረ ጀምሮ ሥጋ ገንዘቡ እንደመሆኑ በሥጋ ይኸንን ሥርዓት ፈጸመ፡፡ ለማይመረመር ለመለኮቱ ባሕርይ እንደሚገባ ደግሞ እርሱ ኅብስት አበርክቶ ሁሉን ያጠግባል፡፡ አይራብም፣ አይጠማም፣ አይደክምም፣ አያንቀላፋም፣ አይታመምም፣ አይሞትም ሕይወትን ለሁሉ ይሰጣል፡፡ ዳግመኛ በዚያ በሲኦል ተገዝተው ያሉ ነፍሳትን ያድን ዘንድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወረደ በመለኮቱም ሲኦልን በዘበዘ፡፡
ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ የወልድን ነገር በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ አለ
እጆቹን፤ እግሮቹን በተቸነከረባቸው ችንካሮች መወጋቱንም እናምናለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ እኛን ለማዳን ኃጢአታችንንም ለማስተስረይ መከራ ተቀበለ እንዳለ፤ በባሕርዩ ሕማም የሌለበት ሲሆን በሥጋ የታመመ ነው፡፡ በእርሱ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ድነናል አለ፡፡ በተገረፈና በተቸነከረም ጊዜ በመከራው ሁሉ መለኮትን ሕማም ተሰማው የሚል ሰው ቢኖር የተለየ የተወገዘ ይሁን፡፡
የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ዲዮናስዮስ 
የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ዲዮናስዮስ ከላከው ሲኖዶሳዊ መልእክት የተገኘ እርሱ መቼም መች ከመለኮቱ ሳይለይ የሰውነትንሥራ ሁሉ ገንዘቡ አደረገ፡፡ ይኸውም መራብ፣ መጠማት፣ መንገድ በመሔድ መድከም፣ በመስቀል ላይ መሰቀል፣ በብረት ችንካር መቸንከር ነው፡፡ በሰውነቱ መቸም መች ሰው ነው፣ በአምላክነቱም ሰውን የፈጠረ ነው፡፡ ግን ከማይከፈል ተዋሕዶ በኋላ መከፈል የለበትም፡፡ ሰው እንደ መሆኑ ስለ እኛ የታመመው የሞተውእርሱ ነው፡፡ በመለኮቱ ግን መቸም መች አይታመምም አይሞትም፣ ሕማምንና ሞትንም አይቀበልም፡፡ በሞቱ ሞትን ያጠፋው እርሱ ነው፡፡ ሲኦልንም የበዘበዘው እርሱ ነው፡፡
የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ሐዋርያው ቅዱስ አትናቴዎስ
 እንዲህ አለ ነፍሱን ከሥጋው በለየ ጊዜ ያን ጊዜ በሲኦል ፈጥኖ ብርሃን ታየ፡፡ ጌታችን በአካለ ሥጋ ያይደለ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሔደ፡፡ ሲኦል ተነዋወጠች፣ መሠረቶቿም እፈርስ እፈርስ አሉ፣ ምድርን ያለ ጊዜዋ እንዳታልፍ ክብርት ደሙን በምድር ላይ አፈሰሰ፡፡ ከኅልፈት ጠበቃት በርሷ ያለውንም ሁሉ ጠበቀ፡፡ ስለ ፍጥረት ሁሉ ሥጋውን በመስቀል እንደተሰቀለ ተወው፡፡ ነፍሱ ግን ወደ ሲኦል ወረደች ከዚያ ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን አዳነች፤ ሲኦልንም በዘበዘች፤ ፍጥረትንም ሁሉ ገንዘብ አደረገች፡፡ ሥጋውም በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትንፈታች፡፡ ሃይማኖታቸው የቀና ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ሊቃውንት በአንድ ልብ እንዲህ አሉከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ የተፈጠረያይደለ፣ በባሕርዩ ከአባቱ ጋር አንድ የሚሆን፡፡ ሁሉ የተፈጠረበት ያለ እርሱ ግን ምንም ምን የተፈጠረ የሌለ፣ በሰማይ በምድር ያለውም ቢሆን፡፡ እኛን ስለማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በግብረመንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ፡፡ የሠላሳ ዘመን ጎልማሳ ሆኖ በጶንጦስ ሰው በጲላጦስ የሹመት ዘመን ስለ እኛ ተሰቀለ፣ ስለ እኛም ታመመ ሞተ ተቀበረ፡፡
የቂሣርያ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ባስልዮስ እንዲህ አለ
ምትሐት ያይደለ በእውነት ተራበ፣ ተጠማ እንጂ፡፡ ዳግመኛም ከኃጥአን ከመጸብሐን ጋር በላ ጠጣ፣ ያቀረቡለትንም በላ፡፡ ራሱን አሳልፎ ለመስቀል ሰጠ፣ እጁን እግሩን ተቸነከረ፣ ጎኑን በጦር ተወጋ፣ ከእርሱም ቅዱስ ምስጢር የተገለጠበት ደምና ውኃ ፈሰሰ /ወጣ/፡፡ የኑሲስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ እንዲህ አለ የሚሠዋ በግ እርሱ ነው፣ የሚሠዋ ካህን እርሱ ነው፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም መሥዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው፡፡ በፈቃዱ መከራን በሥጋው የተቀበለ መከራንም ሁሉ የታገሠ እርሱ ነው፡፡ እንደ በግ ሊሠዋ መጣ፣ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንዳይናገር አልተናገረም፣ በአንደበቱ ሐሰት አልተገኘበትም፡፡ ሰማዕት የሆነ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ፊልክስ እንዲህ አለ በሥጋ መወለድ፣ በመስቀል መከራ መቀበል፣ መሞት መነሣት፣ ገንዘቡ የሆነ እርሱ እግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ስለዚህ በመስቀል ላይ ሳለ ከጥንት ጀምሮ በመቃብር ያሉ ሙታንን ሁሉ አስነሣ፡፡
      የስምኦን ዓምዳዊ ጸሎት
ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ.! በእንጨት
መስቀል ላይ ራቁትሕን የሆንክ ጨለማን
ከለበሰና ስሕተትን ከሚያመጣ የሰይጣን
መንፈስ ለየኝ። በኃይልህ እታደስ ዘንድ
በጥበብህም እመገብ ዘንድ የሕይወት ሐር
ልብስ አልብሰኝ።
ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ. ! መላእክትን
የብርሃን መጎናጸፊያ የምታጎናጽፋቸው.
ኃይልንም የምታስታጥቃቸው በመስቀል ላይ
ራቁትህን ቆምክ።
ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ.! የከበሩ እጆችህን
በእንጨት መስቀል ላይ የዘረጋህ ፍቅርህ
በውስጡ ያድርበት ዘንድ ልቡናየን እንዲከፈት
አድርገው።
ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ.! ማኅየዊ
መስቀልህን አቅፌ ከእርሱ የሕይወትና
የመድኃኒት መዓዛ አሸት ዘንድ ስጠኝ።
በልቡናየም ውስጥ ንጹሕ ደምህ ይውረድ
ንጹሕ መሠዊያ ይሆን ዘንድ ልቡናየን...

ምንጭ፡-
·         ስምዐ ተዋሕዶ፤ ሚያዝያ 1-5 ቀን 2004 ..
·         ማሕበረ ቅዱሳን ገጽ

·         መምህር ለይኩን ብርሐኑ ፌስቡክ ገጽ

0 አስተያቶች:

Post a Comment

Facebook Twitter Addthis Google+