ቀዳሚ ገጽ » » ሆሣዕና (መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ)

ሆሣዕና (መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ)

Written By bahir dar city foot ball club on Friday, April 3, 2015 | 12:31 PM

ይሕ ጽሁፍ በ መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (PhD Candidate) የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት ትርጓሜ መምህር  የተዘጋጀ ሲሆን በመምሕሩ ሙሉ ፈቃድ በጡመራችን ላይ እንዲለጠፍ ተደርጓል

ሆሣዕና ማለት የዕብራይስጥ ቃል ሲኾን “ሆሻአና” ሲባል ትርጒሙም “አቤቱ አኹን አድን” ማለት ነው፤ ይኽ በዓለ ሆሣዕና ከ9ኙ ዐበይት የጌታ በዓላት ውስጥ ሲኾን ኪሩቤል ሱራፌል በፍርሀት በረዐድ ኹነው ዘፋኑን የሚሸሙት ጌታ በትሕትና በአህያና በውርንጫይቱ በትሕትና ተቀምጦ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት፣ የዘካርያስ ትንቢት የተፈጸመበት፣ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው የዘመሩበት፣ ሕጻናት በንጹሕ አንደበታቸው ሆሣዕና ብለው ያመሰገኑበት ታላቅ በዓል ነው፡፡

ይኽም ታሪክ በ4ቱ ወንጌላት ላይ ሲጻፍ በማቴ 21፡1 ላይ “ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ” ይላል ቤተ ፋጌ ማለት የበለስ ቤት ማለት ሲኾን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በሚወስደው መንገድ አቅራቢያ ያለች ትንሽ መንደር ስትኾን ኹሉን ዐዋቂ የኾነው ጌታ ጴጥሮስንና ዮሐንስን “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ” ብሏቸዋል፡፡

“ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል” በማለት የኹሉ ፈጣሪ የኹሉ ጌታ መኾኑን አመለከታቸው፤ በተሰጣቸው ሥልጣነ ክህነት የሕዝቡንም የአሕዛቡን ኀጢአት የማሰር የመፍታት ሰማያዊ ሥልጣነ ክህነት የተሰጣቸው ሐዋርያትን የሕዝብ ምሳሌ የኾነችውን አህያይቱንና የአሕዛብ ምሳሌ የኾነችው ውርንጫዋንም አመጡለት፥ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ”

በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ኮርቻ ሳይኾን ልብስ ማድረጋቸው ኮርቻ ይቈረቊራል ልብስ ግን አይቈረቊርምና የማትቈረቊር ሕግ ሠራኽልን ሲሉ፤ ዳግመኛም ልብስ በአካል ያለውን ኀፍረት እንዲሰውር አንተም በደላችንን የምትሰውርልን ይቅር ባይ ነኽ ሲሉ፡፡
ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ 16 ምዕራፍ ሲኾን መተርጒማን እንደሚገልጹት 14ቱን ጌታ በእግሩ ሲኼድ 2ቱን በአህያዋ፤ በውርንጫዋ 3 ጊዜ ቤተ መቅደሷን ዞሯል፡- 14ቱ በእግሩ መኼዱ የ10ሩ ቃላት 4ቱ የ4ቱ ኪዳናት ምሳሌ፡፡ 2ቱ በአህያዋ መጓዙ የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ፤ 3ቱን በውርንጫዋ ተቀምጦ ቤተ መቅደሱን መዞሩ የ3ትነቱ የአንድነቱ ምሳሌ ነበር፡፡

ክብር ይግባውና ጌታ ንጉሠ ነገሥት ሲኾን፤ ኪሩቤል ሱራፌል ዙፋኑን በፍርሀት በረአድ የሚሸከሙት 24ቱ ካህናተ ሰማይ ዙፋኑን በፍርሀት የሚያጥኑለት ርሱ በትሕትና የዋህ ኾኖ በተናቁት በአህያና በውርንጫይቱ ላይ ተቀመጠ፤ ይኽም የተናቁትን ሊያከብር እንደመጣና፤ በየዋሀን ምእመናን ልቡና እንደሚያድር ለማሳወቅ በነርሱ ተቀመጠ፤ በአህያ የተቀመጠ አባሮ እንደማይዝ ሸሽቶ እንደማያመልጥ ርሱም ካልፈለጉት እንደማይገኝ ከፈለጉት እንደማይታጣ በምስጢር አመለከታቸው፡፡

ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፡- ስለዚኽ ነገር በትርጓሜ ወንጌሉ ላይ “እነዚኽ እንስሳት መላውን የሰው ልጅ ይወክላሉ፡፡ ኹለቱም አህያ መኾናቸውም የሰው ልጅ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበረውን አኳኋን የሚያስረዳ ነው፡፡ ምክንያቱም አህያ በኦሪቱ ዘንድ ንጹሕ እንስሳ አይደለችም፤ ብዙ ክብደት ያላት የማትወደድ እንስሳ ናት፤ ዲዳ ናት፤ ደካማ ናት፡፡ ሰውም እንደተናገርን ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት እንዲኽ ነበረ፡፡” በማለት ሲያመሰጥር ሊቁ ቅ. ቄርሎስ ዘእስክንድርያም፡- “ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ጠቢብ አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ማሰብና ማሰላሰል የሚችል ፍጥረት አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ሰይጣን ግን አታለለው፡፡ ምንም እንኳን ሰው በሥላሴ አምሳል ቢፈጠርም መልኩን አበላሸው፡፡ ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔርን ማወቅ ተሳነው፡፡ ክፉው ሰይጣን ሰውን እንስሳ እስኪመስል ድረስ ክብሩን አዋረደው፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት፡- “ሰውስ ክብሩን አላወቀም፤ የሚጠፉ እስሳትን መሰለ” ያለውም ስለዚኹ ነው /መዝ.49፡12/፡፡ በመኾኑም አህያይቱ ክብራቸውን አጥተው ተዋርደው የነበሩትን እስራኤል ዘሥጋን ትመስላለች፡፡ እስራኤል ከሕጉ ጥቂት ነገርን ያውቃሉ፡፡ ከነቢያትና ከቅዱሳንም ትንሽ ያውቃሉ፡፡ ከኹሉም በላይ ደግሞ ወደ አሚን የሚጠራቸውን ክርስቶስን አልታዘዙትም፡፡ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ሲላቸውም እንደምን እንደ አሕያይቱ በድንቁርና ተይዘው እንደነበረ ሲገልጥላቸው ነው፡፡ ውርንጫይቱ ደግሞ አሕዛብን ትወክላለች፡፡ ውርንጫ እኽልን ለመጫን እንደማታገለግል ኹሉ አሕዛብም ማኅደረ እግዚአብሔር ከመኾን ርቀው ነበርና፡፡” በማለት ገልጽዋል፡፡

ሊቁ ጀሮምም፡- “ደቀ መዛሙርቱ አህያይቱንና ውርንጫይቱን ለመፍታት ኹለት ኾነው መላካቸው ለሕዝብም ለአሕዛብም መላካቸው ያመለክታል፡፡” • አምብሮሲስ፡- “አህያየቱን ለመፍታት ማንም አይከለክላችኁም ብሎ መላኩ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ሥልጣን ሰማያዊ መኾኑ ያመለክታል፡፡” በማለት ልዩ ምስጢርን አስተላፎበታል፡፡
ያን ጊዜ ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ ይኽንም ማድረጋቸው ስንኳን አንተ የተቀመጥኽባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባኽም ሲሉ ነበር፤ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር
ይኽም ዘንባባ ብዙ ምሳሌ ያለው ነው፤ ይኸውም በእስራኤል ያለው ሰሌን፣ ተምር፣ ዘይት ነበርና ያነን ቈርጠው አመስግነውታል፤ ይኽም ምሳሌነት ያለው ነው፤ ይኽም ሰሌን እሾኻማ እንደኾነ ትእምርተ ኀይል ትእምርተ መዊእ አለኽ ሲሉ ነው፤ እሳት ለብልቦ ይተወዋል እንጂ እንደማያቃጥለው ባሕርይኽ አይመረመርም ሲሉ ነበር፡፡

ዳግመኛም ከሰሌን ዝንጣፊ ጋር ተመሳሳይ ተምር ይዘዋል ይኽም ተምር ልዑል ነው አንተም ልዑለ ባሕርይ ነኽ ሲሉ፤ ፍሬው አንድ እንደኾነ አንተም ዋሕደ ባሕርይ ነኽ ሲሉ፡፡ በእሾኽ የተከበበ ነው ባሕርይኽ አይመረመርም ሲሉ ነበር፡፡

የዘይት ዛፍ ነው ቢሉ ዘይት ጽኑዕ እንደኾነ ጽኑዐ ባሕርይ ነኽ ሲሉ፤ ብሩህ ነው ብሩሀ ባሕርይ ነኽ በትምህርትኽም የሰውን ልቡናን ታበራለኽ ሲሉ፤ ዘይት መሥዋዕት እንደሚኾን መሥዋዕት ትኾናለኽ ሲሉ ነበር፡፡
“የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር” በማለት በአርያም መድኀኒት እንደኾነና እግዚአብሔር አብ “የምወድደው ልጄ ይኽ ነው” ብሎ መስክሮለት የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የሚያርቅ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን የሚያድል መኾኑን ኹሉም መሰከሩለት፡፡

በእጅጉ የሚደንቀው የ40 ቀን የ80 ቀን ሕጻናት የፈጠራቸው ጌታ በአህያና በውርንጫ ተቀምጦ ባዩት ጊዜ በንጹሕ አንደበታቸው አንደታቸው ረቶላቸው ጌታን ዘንባባ በመያዝ ሲያመሰግኑ በእጅጉ ይደንቅ ነበር፤ ነገር ግን ጸሐፍት ፈሪሳውያን ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት፤ ኢየሱስም፦ እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? በማለት በሕጻናት እንደሚመሰገን የነርሱም ጌታ መኾኑን ከዳዊት መዝሙር በመጥቀስ ነገራቸው፡፡

ሊቁ ያዕቆብ ዘሥሩግ ሰለዚኽ ምስጢር ሲገልጸው ፡- “ፍቅርኅ ከዘባነ ኪሩብ አውርዶ በአህያ ዠርባ ላይ እንድትቀመጥ አስገደደኅ፡፡ ብዙ ዓይንና ብዙ ገጽ ካላቸው ከሠራዊተ መላክእት ይልቅ በዲዳዋ አህያ ትመሰገን ዘንድ ወደደክ፡፡ በሰማይ ሠራዊት ሠረገላ ተቀምጠኅ ክብርኅን ማሳየት አልወደድክም፤ በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጠኅ ወደ ሰማይ ሠራዊት መኼድን መረጥክ እንጂ፡፡ በአርያም እሳታውያን የሚኾኑ ኪሩቤል ያመሰግኑኻል፤ በምድርም ሕፃናት ይዘምሩልኻል፡፡ በአርያም ብርሃናውያን መላእክት በብርሃን ክንፋቸው መንገድኽን ያነጥፉልኻል፤ በምድርም ደቀ መዛሙትኽ ልብሳቸውን አንጥፈው መንገድኽን አስተካከሉ፡፡ ወዮ! አርያማዊ ሲኾን ምንም ሳይንቀን ይጐበኘን ዘንድ ከአባቱ መጣ፡፡ እርሱም በገዛ ፈቃዱ ሰው እስከ መኾን ደርሶ መጣ፡፡ በአህያ ላይ ተጭኖም ይጐበኘን ዘንድ መጣ፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ የመንፈስ ቅዱስን እንዚራ ይዞ በደስታ ትንቢትን ለመናገር ይቻኰላል፡፡ እየደረደረም የጽዮንን ልጅ ይጠራታል፡፡” በማለት አስተምሯል፡፡

ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት የኾነችው በደመ ወልደ እግዚአብሔር የተመሠረተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ይኽነን በዓል በታላቅ ድምቀት፣ በማሕሌት፣ በቅዳሴ በተለይም ጌታ ቤተ መቅደሱን እየተመሰገነ መዞሩን በማሰብ በአራቱ መኣዝነ ቤተ ክርስቲያን ምስባክ እየተሰበከ ወንጌል እየተነበበ ከጾመ ድጓ ምራት እየተመራ በታላቅ ድምቀት በዓሉ ሲከበር፤ ሕዝበ ክርስቲያኑም በተመስጦ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዞ በግንባሩ አስሮ “ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት” በማለት ፈጣሪያቸውን የባሕርይ አምላክ የኾነውን ንጉሠ ነገሥት፣ አምላከ አማልክት፣ የጌቶች ጌታ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተካከለውን ፈራጅ የኾነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያመሰግናሉ፡፡
               ከበዓለ ሆሣዕና ረድኤት በረከት ያሳትፈን፡፡

                                 ©መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ

0 አስተያቶች:

Post a Comment

Facebook Twitter Addthis Google+