ቀዳሚ ገጽ » » የአድዋው ጦርነት ዘመቻና ዝግጅት

የአድዋው ጦርነት ዘመቻና ዝግጅት

Written By bahir dar city foot ball club on Wednesday, March 18, 2015 | 8:46 AM

ምንልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ                                                           ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ ሐበሻ                                                                                                    
አፄ ምኒልክ መስከረም 7 ቀን 1888 . ከዚህ ቀጥሎ ያለውን የክተት አዋጅ በይፋ በነጋሪት አስነገሩ፡፡
‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላትን አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛኹ፡፡ እንግዲህ ብሞት ሞት የሁሉም ነውና ስለ እኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም ያገሩን ከብት ማለቅ የሰውን ድካም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡


‹‹አሁንም በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ዕርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህም ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን ዕርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፣ አልተውህም ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ፤ አሉ፡፡

የሩቁንም አገር የጎጃሙንም፣ የደንቢያውንም፣ የቋራውንም፣ የበጌምድሩንም ከጨጨሆ በላይ ያለውን አገር ሁሉ አሸንጌ ድረስ ክተት ብለው አዘዙ፡፡ የሰሜንና የወልቃይት ጠገዴንም ሰው መቀሌ ድረስ ክተት ብለው አዘዙ፡፡ ከዚህ በኋላ ራስ መኮንን የሐረርጌን ጦር ይዘው በመስከረም እኩሌታ አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ከጊቤ በታች ያለው አገር ጦር የወለጋው ሹም ፊታውራሪ ተክሌ ጦራቸውን ይዘው ገቡ፡፡ አፄ ምኒልክ አዋጃቸውን በመስከረም ወር ካስነገሩ በኋላ ለአገር ጥበቃ አጎታቸውን ራስ ዳርጌ ሣህለ ሥላሴን ሾመው እርሳቸው በጥቅምት 2 ቀን 1888 . ከአዲስ አበባ ተነስተው በጊዳ በኩል አድርገው ጥቅምት 18 ቀን ወረይሉ ከተማ ገቡ፡፡ ከዚያም ራስ ሚካኤልን፣ ራስ ወሌን፣ ራስ መኮንንን፣ ራስ መንገሻ አቲከምን፣ ራስ አሉላን፣ ዋግሹም ጓንጉልን፣ ደጃች ወልዴን፣ ፊታውራሪ ገበየሁን፣ ፊታውራሪ ተክሌን፣ ሊቀ መኳስ አድነውን፣ ቀኛዝማች ታፈሰን ‹‹ቀድማችሁ ወደ አላጌ ዝመቱ የሚቀላችሁ ከሆነ ወጉት፡፡ የሚከብዳችሁ ከሆነ ላኩብኝ፤›› ብለው አስቀድመው መላካቸውን ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ ሲያረጋግጡ፣ አንዳንድ ጸሐፊዎች ደግሞ፣ ‹‹እኔ እስክመጣ ድረስ ከባችሁ ተቀመጡ እንጂ አትዋጉ፤›› በማለት ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ያመለክታሉ፡፡

ወደ አድዋ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ቁጥር ብዛቱ በትክከል አይታወቅም፤ ብዙ የታሪክ ጸሐፊዎችም የጻፉት የተለያየ ቁጥር ነው፡፡ ቶኪ የተባለው ጸሐፊ የኢትዮጵያ ወታደሮች ቁጥር 70,000 እስከ 80,000 ይደርሳል ይልና ከእነዚህ ውስጥ ጠመንጃ ያላቸው 25,000 ሰዎች ብቻ ናቸው ብሏል፡፡ አንቶኔሊ ደግሞ 110,000 እስከ 120,000 ይደርሳል ሲል፣ ባራቴሪ እንደጻፈው ደግሞ 75,000 እስከ 80,000 ይደርሳል ብሏል፡፡ ኢልግ 150,000 ነው ሲል ዌልድ ደግሞ በምኒልክ ጥሪ የተሰበሰበው 200,000 ሰው ነው ካለ በኋላ፣ ‹‹ይኼ ሠራዊት በሙሉ ከጦርነቱ ቦታ አልደረሰም፡፡ ሠራዊቱ በከፊል ገና በጉዞ ላይ እንዳለ ጦርነቱ አለቀ፤›› ይላል፡፡
በርከት ያሉ ፀሀፊወች የተስማሙበት የዘማቾች ቁጥር ግን እንደሚከተለው ነው
Ø  አጼ ምንሊክ 30000 እግረኛ 1200 ፈረሰኛ
Ø  እቴጌ ጣይቱ 3000 እግረኛ 6000 ፈረሰኛ
Ø  ራስ መኮንን 15000 እግረኛ
Ø  ራስ መንገሻ ዮሐንስ 12000
Ø  ራስ ሚካኤል 6000 እግረኛ 10000
Ø  ራስ አሉላ 3000 እግረኛ
Ø  ራስ መንገሻ አቴከም 6000 እግረኛ
Ø  ራስ ወሌ 10000 እግረኛ እና 15000 ወደ አውሳ የዘመቱ ነበሩ

ስለ ኢትዮጵያ ጦር ጉዞ  የጻፈው አውሮፓዊው ፓውሎቲ እንዲህ ሲል ዘመቻውን በስዕላዊ መንገድ ገልጿል፡፡ ‹‹የኢትዮጵ ሠራዊት ሲጓዙ በደንብ ተመልክቻለሁ፡፡ ዳገቱን ሲወጡ፣ ቁልቁለቱን ሲወርዱ፣ ሸለቆውን ሞልተው ሲሄዱ በታላቅ ወኔ እየጩኹ፣ እየፎከሩና እየሸለሉ ነው፡፡ ለውጊያ የሚሄዱ አይመስሉም፡፡ ወንዶች፣ ሴቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ቄሶችና መነኮሳት…  ሁሉ ሳይቀሩ በአንድነት ሲጓዙ እኔ እንዳሰብኩት ለጦርነት የሚሄዱ አይመስሉም፡፡ ሕዝብ በሙሉ ተነቅሎ ለወረራ የሚሄድ ይመስላል፤ብሏል፡፡
ሞልቴዶ ደግሞ "…. .አሕያው በቅሎው ፈረሱ ሰው ሁሉ በአንድነት ይዛል መንገድ ሲጠብ መንገድ ይሰራሉ በአንድ ጊዜ በግራ ወይም በቀኝ ይሰማሩና የጠበበውን መንገድ ይሰራሉ ሠራዊቱም ባለፈበት መንገድ እርጥብ የሳር ዘር እንን አይገኝም ምክንያቱም  በ መቶ ሺ የሚቆጠር እግር ረጋግጦ ስለሚያቦካው ነው "
እንዲሕ እንዲሕ እያለ ወደጦርነቱ ጉዞው በተጀመረበት ወቅት አንድ አዲስ ደስ የሚያሰኝና በኢትዮጵያዊነት እሚያስመካ ጉዳይ በህዳር 24 ቀን 1988 ዓ.ም ተፈጸመ ። ይኸውም ደጅአዝማች ጓንጉል ጸጋየ በአፄ ምንሊክ ላይ ሸፍተው ከምንሊክ ጭፍሮች ጋር በጦርነት የተፈታተኑ ሰው ነበሩ ። በዚህም በአድዋ ዘመቻ ጊዜ በምንሊክ ሸፍተው በረሃ እንደገቡ ናቸው ። ምንሊክ ህዳር 24 ቀን መርሳ ላይ ሰፍረው ሳሉ የደጃዝማች ጓንጉል መልዕክተኛ ከአፄ ምንሊክ ዘንድ መጣ ። መልዕክተኛውም " ጃንሆይ ከእርስወ ተጣልቸ በረሃ  ገብቻለሁ አሁን ግን በሐገሬ ላይ የውጪ ጠላት ስለመጣባት የርስዎና የኔ ጉዳይ ቀርቶ ይማሩኝና ወጥቼ ከእርስዎ ከጌታየ ጋር ሆኜ ያገሬን ጠላት ልውጋ ብለዋል።" ብሎ ተናገረ ምኒልክም ተደስተው "ይምጣ ምሬዋለሁ"  ብለው ላኩ። ደጃዝማች ጓንጉልም መጥተው ካፄ ምኒልክ ጋር ተገናኙ ሠራዊቱም መኳንንቱም ያለ ጊዜ ከጌታየ ጋር ልሙት በማለታቸው እጂግ ተደነቁ
    
ይቀጥላል
Ø  የአድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ብሥራት



0 አስተያቶች:

Post a Comment

Facebook Twitter Addthis Google+