ቀዳሚ ገጽ » » መፃጉዕ (የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት)

መፃጉዕ (የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት)

Written By bahir dar city foot ball club on Wednesday, March 18, 2015 | 9:27 AM

በዚህ የአራተኛ የአብይ ጾም ሳምንት አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያዩ ቦታዎች የተለያዩ በሽታዎች ያሏቸውን ሰዎች ፈውስ እንደሰጣቸው ይሰበክበታል።
በተለይም ለእነዚህ በሽተኞች ጌታችን ፈውስን ያደረገላቸው በሰንበት በመሆኑ በሰንበት መልካም ሥራን መሥራትን፤ የታመመ መጠየቅን፤ ያዘነ ማጽናናትን፤ የደከመ መርዳትን፤ የነፍስ ረሐብ ያለበትን በቃለ እግዚአብሔር ማበርታትን እና ተመሳሳይ ሥራዎችን መሥራት ተገቢ እንደሆነም ይሰበክበታል። የሰንበት ቀን የተቀደሰች ዕለት ናትና በሰንበት ክርስቲያኖችን ማበርታት፣ መጠየቅ እና ለሕይወታቸው ተገቢውን መንገድ የምናሳይበት እንጂ የግል ሥራ የምንሠራበት አለመሆኑም ይሰበክበታል። አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰንበት መልካም በማድረጉ ከአይሁድ እና ከፈሪሳውያን ፈተና ቢገጥመውም በሰንበት መልካም ከማድረግ ግን ወደ ኋላ አላለም። እኛም በሰንበት የቤተ ክርስቲያንን ነገር ብቻ እንድናደርግ በማሰብ በሰንበት ያልተፈቀደውን ትተን የተፈቀደውን ብቻ ለማድረግ የተዘጋጀን መሆን ይገባናል።
«ተንሥዕ ንሣዕ ዓራተከ ወሑር፤ ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» /ዮሐ.58/  «ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» ያለው ሠላሳ ስምንት ዓመት በአልጋ ላይ ሰውነቱ ልምሾ ሆኖ ታሞ የነበረውን ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው የህመሙ ዘመን ስለረዘመ ዘመዶቹ ሁሉ እየሰለቹ የማስታመሙን ነገር ችላ ብለው ጥለውት ሄደዋል፡፡ ህመምተኛው ዘመዶቹ በተውት ቦታ በቤተሳይዳ መጠመቂያ ፀበል አጠገብ ተኝቶ ነበር፡፡
ጌታችንም ብዙ ዘመን ተኝቶ እንደኖረ አውቆ «ልትድን ትወዳለህንአለው፡፡ እርሱም መጠቂያው ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም በማለት መልስ ሰጠ፡፡ ፀበሉን አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ድንገት ሲያናውፀው ቀድሞ ወደ ፀበሉ የገባ ይድን ስለነበር፤ መልሱ የሚያመለክተው ከሁሉ ቀድሞ እኔን ተሸክሞ ወደ ፀበል ሊያስገባኝ የሚችል ዘመድ ስለሌለኝ እንዴት እድናለሁ ነበር፡፡
ነገር ግን ጌታችን የሁሉም መድኃኒት በመሆኑ ወዲያው «ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» ሲለው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፡፡ አይሁድ ማን አልጋውን ተሸክሞ እንዲሄድ እንደፈቀደለት ቢጠይቁት ለጊዜው ጌታችንን ባያውቀውም፤ በሌላ ጊዜ ጌታችን ሲያገኘው «እነሆ! ድነሃል ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ዕወቅ» በአለው ጊዜ ይህ ሰው ከሰላሳ ስምንት ዓመት የአልጋ ቁራኝነት በኋላ ከተጣበቀበት አልጋ ያላቀቀውን አምላክ ረስቶ ለአይሁድ ሊጠቁመው ሮጦ ሄደ፡፡ እንዳሰበውም ነገራቸው እነሱም ሊያሳድዱት ሊገሉትም ይሹ ነበር፡፡
ከዚህ የፈውስ ታሪክ ፈርጀ ብዙ ነገር እንረዳለን፡፡ ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን እንመልከት፡-
1.  እግዚአብሔር ሕሙማንን በምሕረቱ ይጐበኛቸዋል፤ ከደዌአቸውም ፈውሶ ጤንነታቸውን ሊመልስላቸው ይችላል፡፡
 ከታሪኩ እንደተመለከትነው ሠላሳ ስምንት ዓመት የተኛውን ከደዌው፣ ከእናቱ ማህፀን ያለዓይን የተወለደውን ከዓይነ ስውርነት፣ አስራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረችውን ከሕመሟ፣ ከሞተ አራት ቀን የሆነውን አልአዛርን ከሞት፣ የመቶ አለቃውን ልጅ ባለበት ሆኖ ከሞት ወዘተ አድኗቸዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው እምነታችን ካለንና እግዚአብሔር ከፈለገ ማዳን እንደሚቻለው ነው፡፡
2.  የዳነ ሰውም ያዳነው አምላኩን በማወቅ፤ ውለታውን በሃይማኖት ጸንቶ በደግ ሥራ መመለስ ይገባዋል፡፡
 በመጻጉዕ ታሪክ ላይ ግን የምናገኘው እንዲህ አይደለም፡፡ ከተጣበቀበት የአልጋ ቁራኛነት እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ቢያድነው፤ ለአይሁድ አለቆች ባዳነው ሰውነቱና እግሮቹ ሮጦ ሄዶ ሰብቅ ሠራ፡፡ ምስክር ይሆንበት ዘንድ «እነሆ ድነሃል ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ» በማለት እየተናገረው ሳለ «በሰንበት ያዳነኝ ኢየሱስ ነው» በማለት ያዳነውን በመክሰስ አሳልፎ ሰጠው፡፡ የሰውየውን ማንነት ስንመለከት ልቡ ያልዳነ፤ ያዳነውን ሊረዳ ያልቻለ፣ ክፉና ደጉን ማገናዘብ የተሳነው ሰው ነው፡፡ ዛሬስ ለተደረገልን መልካም ነገር ተገቢውን መልካም ምላሽ በበጐነት የመለሰን ስንቶቻችን ነን?

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳን አምላክ ላደረገላቸው ፈውስ ዘመናቸውን በበጐ ምግባር የፈፀሙ አያሌ ቅዱሳን አሉ፡፡ ለምሳሌ ክፉ መናፍስት አደረውባት የነበረችና በኋላ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምህረት እጁ የጎበኛትን መግደላዊት ማርያምን መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ ይህች ሴት ሰባት አጋንንት የወጣላት ሴት ስትሆን ጌታችን በሚያስተምርበት እየዞረች ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን በጉልበቷና በገንዘቧ ለጌታችንና ለሐዋርያት የሚያስፈልጋቸውን በማቅረብ ታገለግል ነበር፡፡ /ሉቃ. 8÷2-3/ ፡፡ በትንሣኤው ቀን ማለዳ ከሁሉ ቀድማ ተገኝታለች፤እያለቀሰችም ጌታችንን ትሻው ነበር፡፡ ለዚህም ልዩ ትጋቷ ጌታችን ከሌሎቹ ይልቅ ትንሣኤውን ለማየት የመጀመሪያዋ አድርጓታል፡፡ የምስራቹን ለሐዋርያት በማድረስ በኩል የክብር መልእክተኛ ሆናለች ከዚህ የበለጠ ምን መታደል አለ፡፡ /ዮሐ. 10.1-18/

ከነቢያት አንዱ ነቢዩ ኢሳይያስን ብንመለከት ሐብተ ትንቢቱ ተነስቶት ከንፈሮቹ በለምፅ ነደው እያዘነ ይኖር ነበር፡፡ ኦዝያን በሞተበት ወራት እግዚአብሔር በታላቅ ዙፋን ተቀምጦ ታይቶት፤ ምስጋና ከሚያቀርቡት መላእክት አንዱ ሱራፌል እየበረረ መጥቶ በጉጠት ፍም አፉን ዳሶት «በደልህ ከአንተ ተወገደ፣ ኃጢአትህም ተሰረየልህ» ብሎት ከለምጹ አንጽቶት ኃጢአቱ እንደተሰረየለት ነግሮት ሄዷል፡፡ ነቢዩ ስለተደረገለት ፈውስ የጌታ ድምፅ ማንን እልካለሁ? ሲል እነሆ እኔ አለሁ ብሎ ትንቢት በመናገር፣ ሕዝቡን በማስተማር በመጋዝ እስከ መሠንጠቅ ድረስ እራሱን ለእግዚአብሔር ሰጥቷል፡፡ ከላይ ያየናቸውን ሠላሳ ስምንት ዓመት በአልጋ ላይ የተኛውን መፃጉንና መግደላዊት ማርያምን እንዲሁም ነቢዩ ኢሳይያስን ስናወዳድር በተገቢው ምላሽ ያልሰጠው መፃጉዕ ነው፡፡/.ኢሳ.6÷1-8/፡፡

እኛስ በየደቂቃው በኃጢአት ሳለን እንኳ ጥበቃው የማይለየን እግዚአብሔር ያደረገልንን በማሰብ አሁን በዚህ ሰዓት ምን እየሰራን ይሆን ? ወደፊትስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ምን ለመሥራት አስበናል? ለባሮቹ ፈውስን ሰጥቶ በጐ ምላሽን በማከናወን ያፀናቸው አምላክ እኛንም ይረዳን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ ይቆየን!
       የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
አምላኩሰ ለአዳም ለዕረፍት ሰንበተ ሠርዓ ወይቤልዎ አይሁድ በዓይ ሥልጣን ትገብር ዘንተ ወይቤሎሙ ኢየሱስ አነኒ እገብር አንትሙኒ እመኑ ለግብርየ ወይቤሎሙ አነ ውእቱ እግዚኦ ለሰንበት እግዚኦ ውእቱ ለሰንበት ወልድ ዋሕድ ወይቤሎሙ ብውህ ሊተ እኅድግ ኃጢአተ በዲበ ምድር እስበክ ግዕዛነ ወእክሥት አዕይንተ ዕውራን አቡየ ፈነወኒ
ትርጉም:  “የአዳም ፈጣሪ ለዕረፍት ሰንበትን ሠራ፤ አይሁድም በማን ሥልጣን ይህን ታደርጋለህ አሉት፤ እርሱም እኔ እሠራለሁ እናንተም ሥራዬን እመኑ አላቸው፡፡ የሰንበት ጌታው እኔ ነኝ፤ የሰንበት ጌታው/የአብ/ አንድያ ልጁ ነው፡፡ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር እል ዘንድ ፣ ነፃነትን እሰብክ ዘንድ ተሰጥቶኛል ፣ የዕውራንን ዓይን አበራ ዘንድ አባቴ ልኮኛል አላቸው፡፡” ማለት ነው፡፡

ምንባባት መልዕክታት
ገላ. 5÷1-ፍጻሜ   በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ። እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ። ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም። ሕግንም ሁሉ እንዲፈጽም ግድ አለበት ብዬ ለሚገረዙት ሁሉ ለእያንዳንዶች ደግሜ እመሰክራለሁ። በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል። እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና። በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አልወጣም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል። የተለየ ነገር ከቶ እንዳታስቡ እኔ በጌታ ስለ እናንተ ታምኜአለሁ፤ የሚያናውጣችሁ ማንም ቢኖር ግን ፍርዱን ሊሸከም ነው። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? እንኪያስ የመስቀል ዕንቅፋት ተወግዶአል። የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ። ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ። ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው። ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ። ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።…..  (ተጨማሪ ያንብቡ)
ያዕ.5÷14- ፍጻሜ ምዕ.ከእናንተ የታመመ ሰው ቢኖር በቤተ ክርስቲያን ያሉ ቀሳውስትን ይጥራና ይጸልዩለት፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጸለየበትንም ዘይት ይቅቡት፡፡… (ተጨማሪ ያንብቡ)
ግብረ ሐዋርያት
የሐዋ.3÷1-11  ጴጥሮስና ዮሐንስም በዘጠኝ ሰዓት ለጸሎት በአንድነት ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፡፡ ከእናቱ ማኅፀንም ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደ አንድ ሰው ነበር፤ ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ ሁል ጊዜ እየተሸከሙ መልካም በሚልዋት በመቅደስ ደጃፍ ያስቀምጡት ነበር፡፡… (ተጨማሪ ያንብቡ)
     ምስባክ
መዝ.40÷3  “እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፡፡ ወይመይጥ ሎቱ ኩሎ ምስካቢ /ቤ/ሁ እምደዌሁ አንሰ እቤ እግዝኦ ተሣሃለኒ
ትርጉም፦  እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው የተነሣ ይለውጥለታል፡፡
     ወንጌል
ዮሐ. 5÷1-24  ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል ነበረ፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር። በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ። ልትድን ትወዳለህን? አለው። ድውዩም። ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ። ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ያም ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው። ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም አሉት። እርሱ ግን። ያዳነኝ ያ ሰው። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ ብሎ መለሰላቸው። እነርሱም። አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰው ማን ነው? ብለው ጠየቁት። ዳሩ ግን በዚያ ስፍራ ሕዝብ ሰለ ነበሩ ኢየሱስ ፈቀቅ ብሎ ነበርና የተፈወሰው ሰው ማን እንደ ሆነ አላወቀም። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና። እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው። ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገረ። ስለዚህም በሰንበት ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር። ኢየሱስ ግን። አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው። እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ። እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል። አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።
ቅዳሴ  
    ዘእግዚእነ
                        ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ
Ø  ተዋሕዶ ሃይማታችን በ አባ ዘሚካኤል ደሬሳ

Ø  ዓውደ ምሕረት 

0 አስተያቶች:

Post a Comment

Facebook Twitter Addthis Google+