ቀዳሚ ገጽ » » ዘወረደ የዓብይ ጾም የመጀመርያ ሣምንት

ዘወረደ የዓብይ ጾም የመጀመርያ ሣምንት

Written By bahir dar city foot ball club on Wednesday, March 18, 2015 | 9:16 AM

 «ዘወረደ» ማለትም በቀጥታ፣ ቃል በቃል ሲተረጐም «የወረደ» ማለት ነው፡፡ ይህም በምስጢሩ አምላክ ወልደ አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም በቅዱስ ፈቃዱ ሰው ሆኖ ከሰማየ ሰማያት = ከባሕርይ ልዕልናው በትሕትና ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመላክት፣ ይህም የሚታወስበት፣ የሚወሳበት የዐቢይ ጾም አንደኛው ሳምንት ነው፡፡
ዮሐ.3-13፡፡
እግዚአብሔር በገባዉ ቃልኪዳን መሰረት “…የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” እንዳለ ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስ የጠፋዉን አዳም ፍለጋ ከአባቱ እሪና ሳይጎድል ሳይለይ ከሰማይ መዉረዱን የምናዘክርበት በዓል ነዉ።
‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ›› የሚልና ይህንን የመሳሰለ ጌታ እኛን ለማዳንና ፍቅሩን ሊገልጽልን ከሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም የእኛን ሥጋ መዋሐዱን የሚያዘክር ምስጋና የሚቀርብበት ሳምንት ነው፡፡ ሌላም ስም አለው ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ይህ ጾም የጾም መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት የምንጾመው ጾም ሲሆን ሕርቃል የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
                  ሕርቃል ማን ነው? ለምንስ በስሙ ተሰየመ?
 በ614 ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት አደረሰ፡፡ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው ቤተመቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡ ቢነካው አቃጠለው ዲያቆናቱን አሸክሞ ሌላውን ንዋየ ቅድሳት ዘርፎ 60ሺ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3ሺ የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋንም አቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ ገብተው የተሸሸጉ ተሰብስበው ከ14 ዓመት በኋላ በ628 ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲየኑ የሮም ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል፡፡ እርሱም ሐዋርያት ሰውን የገደለ እድሜውን በሙሉ ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርገው አላቸው እኛ የአንተን እድሜ ተከፋፍለን እንጾማለን ብለው አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው ጾሙን በሚገባ ጾመውታል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ተነሳበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉን ያለበትን አጥቶ ሲቸገር መስቀሉን ሲቀብርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት ሆና ያየችው ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና አሳይታው አውጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ ቁስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡ የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ ይህን ለማሰብ ለማስታወስ በተጨማሪ በኃጢአት ላይ ድል እንድናገኝ መንፈሳዊ ጦር በውስጣችን እንዲበዛልን መስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ እኛንም ከኃጢአት ምርኮ መልሰን ለሕርቃል ድል መንሳትንና በጠላቶቹ ላይ ኃይልን እንደሰጠኸው ለእኛም በኃጢአት ላይ ድል መንሳት መንፈሳዊ ኃይልን ስጠን እያልን እንጾመዋለን፡፡ በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡እዚህ ላይ በዚያን ጊዜ ለሕርቃል ሕዝቡ ሱባኤ ይዞለታል፡፡ ዛሬም እኛ ለቤተክርስቲያን ያደረግነውን በማሰብ እግዚአብሔር አምላክ ለሕርቃል የሰጠውን በጠላቶቹ ላይ ድል መንሳትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ የመጀመሪያውን ሳምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን እንጾማለን፡፡የእኛ ጠላት የጨለማ ገዥ የሆነው ዲያቢሎስ ነውና እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡
ሰዉ የተሰጠዉን የሞት ማስጠንቀቂያ ባለመጠበቁ ፍርድ ተፈርዶበት፣ መዊተ ስጋ መዊተ ነፍስ ነግሶበት፣ በህይወተ ስጋም እያለ በሞት ጥላ ስር የሚኖር እና በሞት ፍርሃት የታጠረ ነበር። ከእግዚአብሔር አንድነት ተለይቶ የተስፋ ቦታዉን ለቆ ከዓለመ መላዕክት ወደ ዓለመ እንሰሳ ተጥሎ የፀጋ ልጅነቱን እና ክብሩን አጥቶ በባርነት ዉስጥ እኩያት ፍትወታት ሰልጥኖበት ይኖር ነበር። (መዝ፡- 18፡4-5)

ምንም እንኳን ሰዉ እግዚአብሔርን ከሰማይ ከመንበሩ የሚያስወርድ ስራ ባይኖረዉም አምላኩን (ወልድን) ከመንበሩ የሚስብ ፍቅር ባይኖረዉም እግዚአብሔር ግን ሰዉን እንዲሁ ወዶታልና ይፈልገዉ ዘንድ ፣ ከወደቀበት ያነሳዉ ዘንድ ወረደ። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ህይወት እንዲኖረውእንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና። ”  (ዮሐ 3፡16) ተብሎ እንደተፃፈ እግዚአብሔር ሰዉን የወደደዉ እንዲሁ ነዉ እንጂ ሰዉ የሚወደድ ነገር ኖሮት አልነበረም።

ሰዉን ከዚህ ሁሉ መከራና ስቃይ አዉጥቶ ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰዉ ዘንድ ከዚያም በላይ ያደርሰዉ ዘንድ አካላዊ ቃል ወልደእግዚአብሔር ወረደ። ሰዉ ሆነ። ይህ ምስጢረ ተዋህዶ ነዉ። ተዋህዶ እንበለ ተፈልጦ (ያለመለያየት) የሌለበት ነዉና አካላዊ ቃል ወርዶ በተዋሃደ ቅፅበት የትስብዕት ወይም የስጋ ዕርገቱ በዚህ ጊዜ ነዉ። ምክንያቱም በምድር  በከርሰ ድንግል እያለ በሰማይ ከአባቱ እና ከሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አልተለያዩምና ነዉ። በዚህም የትስብዕት ዕርገቱ በፅንሰት፣ የቃል ዕርገቱ በዓርባ ቀን  ድህረ ትንሣኤ መሆኑ በዚሁ ዕለት በሚነበበዉ ወንጌል ላይ “ከሰማይ ከወረደዉ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም። እሱም በሰማይ የሚኖረዉ የሰዉ ልጅ ነዉ።” (ዮሐ 3፡13) በሚለዉ የኢየሱስ ክርስቶስ ንግግር በምድር እያለ እየተመላለሰ “በሰማይ የሚኖረዉ የሰዉ ልጅ ነዉ”። ባለዉ አምላካዊ ቃል ይታወቃል። ለዚህ ነዉ ታላቁ ሊቅ አባታችን ቅዱስ ያሬድ እመቤታችንን ባመሰገነበት ድርሳኑ በአንቀፀ ብርሃን ላይ “… ፍጥረትን ሁሉ ሰብስቦ የሚመግብ ጌታቸዉ በብብትሽ (በክንድሽ) ተቀምጦ ጡትሽን እንደ ሕጻን ሲጠባ ባዩ ጊዜ በአርያም ፈለጉና በዚህ ዓለም እንደ ቀድሞዉ ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አገኙት። የጌታ ትሕትናዉን ባዩ ጊዜም ዓይኖቻቸዉን ወደ ላይ ወደ አርያም ከፍ ከፍ አደረጉ፣ ክንፋቸዉንም ዘርግተዉ ለሁሉ ጌታ ላንተ በሰማይ ምስጋና ይገባሃል። እያሉ ጌታቸዉን አመሰገኑ። ” በማለት የተናገረው።

                            መዝሙር
ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ ባኡ ቅድሜሁ በተጋንዮ ወውስተ አ|ዕፃዲሁ በስብሐት አምንዎ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ ወንትፋቀር በበይናቲነ  እስመ ለዓለም ምሕረቱ አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ እስመ ሰንበትሰ በእንተ ሰብእ ተፈጥረት እስመ ለዓለም ምሕረቱ ምሕረተ ወፍትሐ አሐሊ ለከ እዜምር ወእሌቡ ፍኖተ ንጽሕ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ አባግዓ መርዔቱ።

ትርጉም፦ እግዚአብሔርን በመፍራት ተገዙለት ለእርሱ መገዛትም ደስ ያሰኛችሁ። እግዚአብሔር ቸር ምሕረቱም ለዘላለም፣ እውነቱም ለልጅ ልጅ ነው ። እኛስ ሕዝቡ የመሰማሪያው በጎች ነን፡፤ ወደ ደጁ በመገዛት፣ ወደ አደባባዮችም በምስጋና ግቡ፤ ጾምን እንጹም፤ጓደኞቻችንን እናፍቅር፤እርስ በርሳችንም እንፋቀር ። ሰንበት ስለሰው ተሠርታለችና ሰንበትን እናክብር። እውነትንም እንሥራ፤ አቤቱ ምሕረትንና ፍርድን እቀኝልሃለሁ፤ እዘምራለሁ፤ንጹሕ መንገድንም አስተውላለሁ።
                          ምንባባት
መልዕክታት
ዕብ.13÷7-17 የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)
ያዕ.4÷6-ፍጻ. ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡(ተጨማሪ ያንብቡ)
ግብረ ሐዋርያት                         
ሐዋ.25÷13-ፍጻ. ከጥቂት ቀን በኋላም ንጉሥ አግሪጳና በር ኒቄ ወደ ቂሣርያ ወርደው ፊስጦስን ተገናኙት፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)
                             ምስባክ
መዝ. 2፡11 ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ።አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐፅ እግዚአብሔር።
ትርጉም፦ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ።ጥበብን አጽኑአት ፤ እግዚአብሔር እንዳይቆጣ።
                           ወንጌል
ዮሐ.3÷10-24  ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ፤ ነገር ግን አንዴት ይህን አታውቅም?” አለው፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)
                              ቅዳሴ
  ቅዳሴ ዘእግዚእነ
ምንጭ
Ø  ማሕበረ ቅዱሳን ድህረ ገጽ

Ø  ጾምና ምጽዋት

0 አስተያቶች:

Post a Comment

Facebook Twitter Addthis Google+