በአፍሪካ የጦርነት ታሪክ ውስጥ ሁለት የተከበሩና የተደነቁ ጦርነቶች አሉ፡፡ አንደኛው ከሁለት ሺሕ ዓመታት በፊት ሰሜን አፍሪካዊው ሐኒባል አውሮፓውያንን ድል ያደረገበት ጦርነት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከሁለት ሺሕ ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በአድዋው ጦርነት ወራሪውን የኢጣሊያንን ሠራዊት ድል ያደረጉበት ጦርነት ነው፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ንጋት ላይ የአገሬን ነፃነት፣ ክብሬንና ታሪኬን አላስደፍርም ያለ ወገን በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በእብሪት የተወጠረና ለሺሕ ዘመናት ታፍራና ተከብራ በነፃነት የቆየችውን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ያሰፈሰፉ ናቸው፡፡ ዘመናዊ የጦር መሣሪያን እስከ አፍንጫው የታጠቀ የኢጣሊያ የጦር ሠራዊት ከንቱ የሆነ ህልሙን አንግቦ በአድዋው ላይ ተጋጠሙ፡፡
በአድዋው ጦርነት ላይ በጀግንነት ከተዋጉትና ካዋጉት አፄ ምኒልክ፣ የጦር ሹማምንቶቻቸው፣ መኳንንቶቻቸውና ሠራዊታቸው ባሻገር በተለይ የእቴጌ ጣይቱ ጀግንነትና የጦር ብልኃትም በእጅጉ መጠቀስ የሚገባው ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱ በጦር ዕቅድ አመንጪነታቸው፣ በጀግንነታቸውና በጥንካሬያቸው በምሳሌነት የሚጠቀሱ ሴት ነበሩ፡፡ እቴጌይቱ በሳል፣ ብልህ፣ ደፋርና ጀግና ሴት ነበሩም፡፡ በባለቤታቸውን በአፄ ምኒልክ አመራር ወቅትም በፊት ለፊትም ሆነ በጀርባ ሆነው በሳልና ውጤታማ የሆነ አመራር ይሰጡ የነበሩ ታላቅ ሴት እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክሩላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከአውሮፓ አገሮች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ሁሉ በአንክሮ ይከታተሉና ውሳኔ ይሰጡ የነበሩ ታላቅ ዲፕሎማትም ነበሩ፡፡ ለአብነት ያህል የውጫሌ ውልን ፈጽመው እንደማይቀበሉ ለኢጣያዊው መልእክተኛ ለአንቶኔሊ ከማሳወቅም አልፈው እንዲህ ማለታቸው ይነግርላቸዋል፡፡ ‹‹እኔ ሴት ነኝ ጦርነትን አልሻም፡፡ ግን እንዲህ ዓይነቱን ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ፡፡ ለአገሩ ነፃነት ሲል ደረቱን ለጦር እግሩን ለጠጠር የማይሰጥ ኢትዮጵያዊ በዚህ የሌለህ እንዳይመስልህ፡፡ ስለዚህ ከፈለግህ ጦርነቱን የዛሬ ሳምንት ልታደርገው ትችላለህ ሂድ…›› በማለት ለኢጣሊያዊው አንቶኔሊ በአገራቸው ነፃነትና ሉዓላዊነት ላይ ምንም ዓይነት ድርድር እንደማይኖር ቁርጡን የተናገሩ ደፋርና ጀግና ሴት ነበሩ፡፡
እቴጌ ጣይቱ ሴትነታቸው ሳያግዳቸው ከባለቤታቸው ከአፄ ምኒልክ ጋር በጦር አውድማ በመገኘት፣ የጦር ዕቅድ ከማውጣት ባሻገር በጦር ግንባር ተዋጊና አዋጊ የሆኑ ሴትም ነበሩ፡፡ ለአድዋው ድል ወሳኝ የነበረውን የመቀሌውን ምሽግ በማስለቀቅ በኩል የእቴጌ ጣይቱ ምክር ተጠቃሽ ነው፡፡ እቴጌይቱ በመቀሌ ላይ ጠንካራ የሆነ ምሽግ መሽጎ ለቀናት የኢትዮጵያን ጦር ሲፈታተን የነበረውን የኢጣሊያን ሠራዊት የመቀሌውን ምሽጉንና የውኃ ቦታውን አስገራሚ በሆነ የጦር ምክርና ስልት በመያዝ፣ የመቀሌ ምሽግ በኢትዮጵያ ሠራዊት እጅ እንዲወድቅ አድርገዋል፡፡ በወቅቱ ብዙ የተባለለትና የኢትዮጵያ ሠራዊት በምንም ተዓምር ሊደፍረው አይችልም ተብሎ የተነገረለት ጠንካራው የመቀሌ ምሽግ በእቴጌ ጣይቱ ምክር በኢትዮጵያውያን እጅ መግባቱን የሰሙ በኢጣሊያን አገር የሚታተሙ ጋዜጦችም ስለ መቀሌው ምሽግ መለቀቅ ሲጽፉ፣ ‹‹… በአምባለጌ ላይ ተዋርደን በጦር ኃይል ተሸንፈን ለቀቅን፡፡ ታላቅና ጠንካራ ምሽግ ነው የተባለውን የመቀሌውን ምሽግ ደግሞ በውኃ ሰበብ ለቀቅን፡፡ ይኼ የኢጣሊያ መንግሥትን ውድቀት ስለሚያሳይ መንግሥታችን ድል መሆኑን አምኖ ከሐበሻ ምድር መውጣት አለበት፤›› በማለት ጽፈዋል፡፡
እቴጌ ጣይቱ ከባለቤታቸው ከአፄ ምኒልክ፣ ከኢትዮጵያውያኑ የጦር አዝማቾችና ሠራዊታቸው ጋር በመሆን ከተፋፋመው የአድዋው ጦር ግንባር ላይ በመገኘት ጦሩን ሲያበረታቱ የነበሩበትን ሁኔታ ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ በዚህ መልኩ ጽፈውታል፡፡ ‹‹እቴጌ ጣይቱ ጥቁር ጥላ አስይዘው ዓይነ ርግባቸውን ገልጠው በእግር እየተራመዱ በንጉሠ ነገሥቱ ልጅ ወ/ሮ ዘውዲቱና በደንገጡሮቻቸው ታጅበው ወደፊት ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡ ወዲያው የኋላው ወታደር ሲያመነታ አይተው ‹በርታ ምን ሆነሃል ድሉ የእኛ ነውና በለው› ብለው በተናገሩ ጊዜ ወንድ ሴት ሲያበረታው መሸሽ አይሆንለትምና ሁሉም በወኔና በጀግንነት ወደፊት ገፋ፡፡ እቴጌይቱም በዚህ ቀን የሴትነት ባሕሪያቸውን ትተው እንደ ወንድ ወታደሮቻቸውን በቀኝና በግራ አሰልፈው ወደ ጦርነቱ ገቡ፡፡ መድፈኞቻቸውንም በቀኛቸው በኩል ጠምደው እየተኮሱ በመካከል የሚዋጋውን የጠላት ጦር ይቆሉት ጀመር፤›› በማለት ጽፈዋል፡፡
ከአድዋው ጦርነት በፊት በአምባላጌ፣ በደብረ ኃይላና በእንዳ ኢየሱስ በተደረጉት ተከታታይ ጦርነቶች ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ መኮንን፣ መድፈኞቹ ፊታውራሪ ገበየሁና ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ በአኩሪ
ጀብዳቸውና ጀግንነታቸው የሚጠቀሱ የጦር መሪዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለአድዋው ድል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከነበራቸው መካከል ኤርትራውያኑ ባሻ አውአሎምና ጓደኛቸው ገብረ እግዚአብሔር ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እነዚህ ሰዎች ከኢጣሊያን ጋር የወገኑ መስለው ለኢትዮጵያ ጦር መረጃ በማቀበልና የኢጣሊያንን ጦር እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በመከታተልና በመሰለል ለኢትዮጵያ ጦር መረጃ ሲያቀብሉ የነበሩና ለአድዋው ድል ከፍተኛ የሆነ ሚና የነበራቸው ጀግኖች ነበሩ፡፡ የታሪክ መዛግብት ስለ እነዚህ ጀግኖች እንደሚመሰክሩት በአድዋው ጦርነት ወቅት የጄኔራል አልቤርቶኒን ጦር እየመሩ ሌሊት ሲሰወሩ አልቤርቶኒ ‹‹አውአሎም አውአሎም›› እያለ ሲጣራ፣ ‹‹ዝዋዓልካዩ አያውዕለኒ›› ወይም “በዋልክበት አያውለኝ” ብለው በመጥፋት ወደ ኢትዮጵያ ጦር መቀላቀላቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
ባራቴሪ ይጠብቃቸው የነበሩት ባሻ አውአሎምና ባላምባራስ ገብረ እግዚአብሔር በሰጡት የተሳሳተ መረጃ መሠረት ማለትም የኢትዮጵያ ጦር ስንቅ አልቆበት በየአውራጃው ሄዷል፣ በጦር ሠፈሩ ውስጥ በሽታ ገብቶ ብዙ ወታደሮች ሞተዋል፣ የተወሰነው ጦርም አክሱም ጽዮን ሄዷል፣ ሌላውም ወደመጣበት አገር እየተመለሰ ነው፣ ወዘተ በማለት ለባራቴሪ እንደገለጹለት፣ ይህን መረጃ አምኖ የካቲት 22 ቀን 1888 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ጄኔራል ባራቴሪ የኢትዮጵያን ጦር ለማጥቃት የመጨረሻውን ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ በማግስቱም እሑድ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በአድዋ የጦር አውድማ ለእናት አገራቸው ነፃነትና ክብር ሕይወታቸውን ለመስጠት ያልሳሱ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ከጠላቶቻቸው ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው በአፍሪካ ምድር የነፃነትን ክቡር ምስጥር በክቡር ደማቸው በአድዋ ተራሮች ላይ ጻፉ፡፡
የአድዋ ተራራ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለሰው ልጆች ነፃነት በፈሰሰ ክቡር ደም አሸብርቃና ተውባ በአፍሪካና በመላው ዓለም ከፍ ብላ፣ ደምቃና ገና ታየች፡፡ ኢትዮጵያ በልጆቿ አይበገሬነት፣ ተጋድሎና ቆራጥነት በዓለም ምድር ዳግመኛ የነፃነት ምድር፣ የጥቁር ሕዝቦች የአይበገሬነት ተምሳሌት ሆና ዳግም በክብር ተሞሸረች፡፡ የዓለም ጋዜጦች ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ እስያ፣ ከጀማይካ እስከ ካሪቢያን በአንድ ድምፅ ይህን ታላቅ የሆነ የአባቶቻችንን የነፃነት ተጋድሎ ሊያበስሩ ብዕሮቻቸውን ቀሰሩ፡፡ የአድዋውን ድል በመላው ዓለም ያሉ ጋዜጦች ሁሉ በመጀመሪያ ገጻቸው የምኒልክና የጣይቱን ፎቶግራፍ ፊት ለፊት በማውጣት ወሬውን ለዓለም ሁሉ አደረሱት፡፡ እ.ኤ.አ ማርች 7 ቀን 1896 የወጣው ኒውዮርክ ታይምስ የድሉን ታላቅነት በፊት ለፊት ገጹ ዘግቦት ነበር፡፡ መጋቢት 29 ቀን 1896 ዓ.ም የወጣው ሌ ፔቲ ጆርናል የሚባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ የእቴጌ ጣይቱን ምስል በፊት ለፊት ገጹ አድርጎ የአድዋውን ድል ብሥራት በአድናቆት ዘግቦታል፡፡
ማርጀር ፐርሀም የተባለ አውሮፓው ጸሐፊም የአድዋውን ድል በዓለማችን ታሪክ ውስጥ የፈጠረውን ልዩና አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ በዚህ መልኩ ነበር የገለጸው፡፡ ‹‹የአድዋው ጦርነት አንፀባራቂ ድል ኢትዮጵያን በዘመናዊው የዓለም ካርታ ውስጥ ስሟን እንድታስገባ አድርጓታል፤›› ሲል፡፡ እንግሊዛዊው ታሪክ ጸሐፊ በርክሌይ ደግሞ፣
“ሃያ ሺሕ ያህል ወታደሮች ያሉት የአውሮፓ ጦር በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ፡፡ በእኔ እምነት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ አድዋ ያለ ጦርነት የለም፡፡ በእልቂቱ በኩል ሃያ አምስት ሺሕ ሰዎች በአንድ ቀን የሞቱበትና የቆሰሉበት ነው፡፡ ፖለቲካና ታሪክ አበቃ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ታላቅ የተወላጆች ኃይል መነሳቱ ታወቀ፡፡ የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ፡፡ ጥቁሩ ዓለም በአውሮፓውያኑ ላይ ሲያምፅና ሲያሸንፍ የመጀመሪያው መሆኑ ነው፡፡ ሐበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል፡፡ የእኛ ዓለም ገና ቶሮና ኦዲዮን የሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ዘመን ሐበሾች የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበሉ ናቸው፤” … አሁን የሁሉንም ፍላጎት አድዋ ዘጋው በማለት በአድናቆት ሆኖ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
አፄ ምኒልክም በድሉ ቢደሰቱም በሌላ በኩል ደግሞ በከንቱ ለፈሰሰው ደም መፀፀታቸውን ለሙሴ ሸፍኔ በላኩት ደብዳቤ እንዲህ ገልጸውለት ነበር፡፡ ‹‹በጥጋባቸው አድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ፡፡ እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የእነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰስ እያየሁ ድል አደረግኋቸው ብዬ ደስ አይለኝም፤›› በማለት ለሰብዓዊ ፍጡር ያላቸውን ክብር ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካና የመላው ነፃነት ወዳድ ሕዝቦች ሁሉ ድል ነው፡፡ አድዋ ለሰው ልጆች ነፃነት ተሟጋቾችና ለሰብዓዊ መብት ታጋዮች ለእነ ማርክስ ጋርቬይ፣ ለኬንያ የነፃነት አባት ለጆሞ ኬንያታ፣ ለጋናው ንክሩማ፣ ለደቡብ አፍሪካው የፀረ አፓርታይድ ታጋይ ለኔልሰን ማንዴላና ለትግል አጋሮቻቸው፣ በአጠቃላይም ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ የወኔ ስንቅ የሆነና መነቃቃትን የሰጠ ታላቅና አንፀባራቂ ድል ነው፡፡ የአፍሪካ አገሮች ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ ከፍተኛ የሆነ ሚና የተጫወተችው ኢትዮጵያና ለዚህም በመዲናችን ተቋቋመው የትናንቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዛሬው አፍሪካ ኅብረት ይኼን ለጥቁሮች ሕዝቦች ሁሉ የነፃነት ብሥራት የሆነውን ድል በየዓመቱ በድምቀት ሊዘክረው ይገባል፡፡ ለዚህም የአፍሪካ አገሮች፣ የኅብረቱ መቀመጫ የሆነችው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የታሪክ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶች የአድዋ ድል በክብር እንዲዘከርና አድዋ በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ የበኩላችንን ጥረትና ግፊት ማድረግ ይገባናል፡፡
በዐድዋ ዘመቻ የሞቱት
ታላላቆቹና ለጊዜው ስማቸው የታወቀው ከዚህ ቀጥሎ የተጻፉት ናቸው
Ø
ደጃች
በሻህ አቦየ
Ø
ደጃች
ማናየ
Ø
ደጃች
ጫጫ
Ø
ፊታውራሪ
ገበየሁ
Ø
ፊታውራሪ
ተክሌ
Ø
ፊታውራሪ
ዳምጠው ከተማ
Ø
ፊታውራሪ
ወልደ ሚካኤል ቢራቱ
Ø
ቀኛዝማች
ታፈሰ አባይነህ
Ø
ቀኛዝማች
አባይነኸ
Ø
ፊታውራሪ
ሽንኮሩ
Ø
ቀኛዝማች
ተሰማ ወልዴ
Ø
ቀኛዝማች
በሻህ
Ø
ባላምባራስ
በለው
Ø
ባላምባራስ
ሰይፉ
Ø
ባላምባራስ
አደራ
Ø
አቶ
ሙላቱ የፈረስ ዘበኛ
የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊነት
አንድነት ልዩ ህብር የጠላቶቻችንን ‹‹የከፋፍለህ ግዛው›› ተንኮል ሳይበግረው፣ የኢትዮጵያ መሳፍንቶች ጊዜያዊ ጠላትነት፣ ዘር፣
ጎሳ፣ ሃይማኖት፣ ፆታ፣ ወዘተ ሳይለያየው የአንዲት ኢትዮጵያ አንድነትና የሰንደቅ ዓላማችን ክብር ጎልቶ የወጣበት ድላችን ነው፡፡
ስለዚህም በልዩ የነፃነት ክብርና ልዕልና አድዋን ልንዘክረው ይገባናል፡፡
ክብር ለዐድዋ ሰማዕታት ክብር ዛሬ አፌን ሞልቸ
ኢትዮጵያ አንድል ላረጉኝ ጀግኖች ክብር ለእነርሱ በጀግንነት ያለ ፍርሀት ለተዋደቁ አባቶች ክብር ለርሱዋ ጀግና መሸሽን ላርፈራች
እናቴ ክብር ለእነርሱ በመልክ ቀለሜ የበታችነት እንዳይሰማኝ ላረጉ አባቶቸ ክብር ክብር ክብር ለነእርሱ …..
ምንጭ፦
v
የኢትዮጵያ
ታሪክ ከተክለ ጻድቅ መኩሪያ
v
የአድዋ
ድል የጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ብሥራት
0 አስተያቶች:
Post a Comment