ቀዳሚ ገጽ » » ገብርኄር የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሰንበት

ገብርኄር የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሰንበት

Written By bahir dar city foot ball club on Thursday, March 19, 2015 | 2:30 PM

 የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ገብርኄር ይባላል፡፡ ስለ ኄር /ስለታማኝ/ አገልጋይ ያስተማረውን የሚያዘክር ምስጋና ይቀርብበታል፡፡ ይኸውም ማቴ. 2514-30 ላይ ይገኛል፡፡

ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ አቅሙ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ፡፡ አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቆፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ፡፡
ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት ›› አለ፡፡ ጌታውም ‹‹መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባርያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ›› አለው፡፡ ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍኩበት›› አለ፡፡ ጌታውም ‹‹መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታ ደስታህ ግባ›› አለው፡፡
አንድ መክሊት የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤እነሆ፥ መክሊትህ እነሆ›› አለው፡፡ ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፡- ‹‹አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ ካልዘራሁበት እንዳጭድ ካልበተንሁበትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፥ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር፡፡ ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት ዐሥር መክሊትም ላለው ስጡት ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፡፡ የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት›› አለ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡
መክሊት የተባለ ጸጋ ስጦታ ሲሆን እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን የተለያየ ስጦታ ሰጥቶናል፡፡ በተሰጠንም ስጦታ ልናገለግልበት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪ መክሊት ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ የሰማናትን ቃለ እግዚአብሔር ለሌላው ማሰማት ይገባናል ፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ማሰማቱ ብቻ ነው፡፡ በልቦናው አድሮ ሥራ የሚሠራ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

ምስባክ     
መዝ. 39÷8
"ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፡፡
 ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፡፡
 ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ፡፡"
ትርጉም፦ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ መከርሁ፥
 ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው።
 በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ።

ወንጌል
ማቴ. 25÷14-30 “መንገድ እንደሚሄድ÷ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደ ሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት÷ ለአንዱ ሁለት÷ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ሄደ፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ሄደ፤ ነግዶም ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ፡፡ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታዉን ወርቅ ቀበረ፡፡ ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ተመልሶ ተቈጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና፡- አቤቱ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት አተረፍሁ ብሎ አምስት መክሊት አስረከበ፡፡ ጌታውም፡- መልካም÷ አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለውም መጥቶ፡- አቤቱ÷ ሁለት መክሊትን ሰጥተኸኝ አልነበረምን? እነሆ ሌላ ሁለት መክሊትን አተረፈሁ አለ፡፡ ጌታውም፡- መልካም÷ አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ አሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለውም መጣና እንዲህ አለ፡- አቤቱ÷ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ÷ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ስለ ፈራሁም ሄድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፤ እንግዲህ እነሆ÷ መክሊትህ፡፡ ጌታውም መልሶ አለው፡- አንተ ክፉና ሰነፍ አገልጋይ÷ እኔ ካልዘራሁበት የማጭድ÷ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ ታውቃለህን? ገንዘቤን ለለዋጮች መስጠት በተገባህ ነበር፤ እኔም ራሴ መጥቼ ገንዘቤን ከትርፉ ጋር በወሰድሁ ነበር፡፡
 ከዚያ የቆሙትንም እንዲህ አላቸው፤ ይህን መክሊት ከእርሱ ተቀብላችሁ ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ ላለው ሁሉ ይሰጡታልና፤ ይጨምሩለታልም፤ ለሌለው ግን ያንኑ ያለውን ይወስዱበታል፡፡ ክፉውን አገልጋይ ግን÷ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወደ አለ ጨለማ አውጡት፡፡


 ምንባብ
2 ጢሞ.2÷1-15 ልጄ ሆይ÷ አንተም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ በርታ፡፡ በብዙ ምስክሮች ፊት ከእኔ የሰማኸውን ትምህርት ለሌሎች ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች እርሱን አስተምራቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያገለግል በጎ አርበኛ ሆነህ መከራ ተቀበል፡፡ ወደ ሰልፍ የሚሄድ÷ አለቃውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ነው እንጂ የዚህን ዓለም ኑሮ አያስብምና፡፡ የሚታገልም ቢሆን እንደ ሕጉ ካልታገለ አክሊልን አያገኝም፡፡ የሚደክም አራሽም አስቀድሞ ፍሬውን ሊያገኝ ግድ ነው፡፡ ያልሁህን አስተውል፤ እግዚአብሔርም በሁሉ ነገር ጥበብን ይስጥህ፡፡
 በወንጌል እንደምሰብከው÷ ከሙታን ተለይቶ የተነሣውን ከዳዊት ዘር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስበው፡፡ ስለ እርሱም እንደ ወንጀለኛ አስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም፡፡ ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ሕይወትና የዘለዓለም ክብር በሰማያት ያገኙ ዘንድ÷ ስለ ተመረጡት ሰዎች በሁሉ ነገር እታገሣለሁ፡፡ ነገሩ እውነት ነው፤ ከእርሱ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፡፡ ብንታገሥም ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤ ብንክደው ግን እርሱም ይክደናል፡፡ ባናምነውም እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን መካድ አይቻለውምና፡፡
እንግዲህ ይህን አሳስባቸው፤ በቃልም እንዳይጣሉ÷ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፤ ይህ ምንም የማይጠቅም÷ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና፡፡የእግዚአብሔርን ቃል በእውነት አቃንቶ ሲያስተምር እንደማያፍር ሰራተኛ ሆነህ ፣ራስህን የተመረጠ አድርገህ  ለእግዚአብሔር ታቀርብ ዘንድ ትጋ። 
 1 ጴጥ.5÷1-11 እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ÷ የክርስቶስም መከራ ምስክር÷ ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግለዎችን እማልዳቸዋለሁ፡፡ በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋዎች ጠብቁ፤ ስትጠብቁአቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ አይሁን፤ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን፡፡ ለመንጋዉ ምሳሌ ሁኑ እንጂ ሕዝቡን በኀይል አትግዙ፡፡ የእረኞችም አለቃ በተገለጠ ጊዜ የማይጠፋውን የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ፡፡ እንዲሁ እናንተ ጐልማሶች ሆይ÷ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም ትሕትናን ልበሷት፤ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ያዋርዳልና፤ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉትን ግን ያከብራቸዋል፡፡
እንግዲህ በጐበኛችሁ ጊዜ ከፍ ከፍ ያደርጋችሁ ዘንድ ከጸናችው ከእግዚአብሔር ክንድ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፡፡ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት፡፡ እንግዲህ ዐዋቂዎች ሁኑ፤ ትጉም፤ ጠላታችሁ ጋኔን የሚውጠውን ፈልጎ÷ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና፡፡ እርሱንም በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት፤ እንዲህም ያለ መከራ በዓለም በአሉ ወንድሞቻችሁ ሁሉ እንደሚፈጸም ዕወቁ፤ ፍቅርንም አጽንታችሁ ያዙአት፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዘለዓለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችኋል፤ ልባሞችም ያደርጋችኋል፡፡ለእርሱ ክብርና ኅይል እስከ ዘለአለም ይሁን፤አሜን።
የሐዋ.1÷6-8  እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ÷ "ጌታ ሆይ÷ በዚህ ወራት ለእስራኤል ልጆች መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ቀኑንና ዘመኑን ልታውቁ አልተፈቀደላችሁም፡፡ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኅይልን ትቀበላላችሁ፤በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፣በሰማሪያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮቸ ትሆኑኛላችሁ።"

ቅዳሴ
ዘባስልዮስ

ምንጭ
Ø  ኆህተ ብርሐን ሰ/ት/ቤት
Ø  ዓውደ ምሕረት
Ø  አትሮንስ

Ø  መጽሐፍ ቅዱስ

0 አስተያቶች:

Post a Comment

Facebook Twitter Addthis Google+